የዘንድሮው የሀዲያ ብሔር ዘመን መለወጫ “ያሆዴ” በዓል ሲከበር የተቸገሩትን በመደገፍ፣ በመተሳሰብ እና ያለውን ተካፍሎ በመብላት ሊሆን እንደሚገባ ተገለጸ
የ2018 የሀዲያ ብሔር ዘመን መለወጫ “ያሆዴ” በዓል በወረዳ ደረጃ በሾኔ ከተማ ሁለገብ ስታዲየም ተከብሯል።
የ2018 የሀዲያ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች በድምቀት እየተከበረ ይገኛል፡፡ በዚሁ መሠረት በዞኑ የሾኔ ከተማ አስተዳደር እና የምስራቅ ባዳዋቾ ወረዳ መዋቅሮች በጋራ ሆነው በዓሉን በተለያዩ ክዋኔዎች በሾኔ ከተማ ሁለገብ ስታዲየም በድምቀት አክብረዋል።
የሾኔ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አበራ በዶሬ እና የምስራቅ ባዳዋቾ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ሻሜቦ በእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸው ባደረጉት ንግግር ፤ የዘንድሮ የያሆዴ በዓል ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተጠናቆ ከተስፋ ወደሚጨበጥ ብርሃን የተሸጋገርንበት ወቅት ላይ የሚከበር መሆኑ ልዩና ድርብ ደስታ ይሰጣል ብለዋል።
የተጣላ የሚታረቅበት፣ ተራርቀው የሚኖሩ በአንድ ላይ ተሰባስበው በመመራረቅ የሚያከብሩት በብሄሩ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የአደባባይ በዓል ስለመሆኑም ተናግረዋል።
በዓሉ ሲከበር የተቸገሩትን በመደገፍ፣ በመተሳሰብ እና ያለውን ተካፍሎ በመብላት ሊሆን ይገባል ሲሉም አስተዳዳሪዎቹ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
የክረምት ጭጋግና ደመና አልፎ አሮጌውን ዓመት ሸኝተን አዲሱን ዓመት የምንቀበልበት የብሩህ ዘመን ተስፋ የሚሰጥ በዓል ነው ብለዋል።
በበዓሉ በክብር እንግድነት የተገኙት የሀዲያ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ሀኃላፊና የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ተወካይ ወይዘሪት ገነት ሙሉጌታ በበኩላቸው፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተመረቀበት ማግስት እና በኢትዮጵያ ማንሰራራት ዘመን እየተከበረ ያለ በዓል መሆኑን አንስተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላፈዋል።
የዘንድሮ የሀዲያ ብሔር ዘመን መለወጫ “ያሆዴ” በዓል አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች እና በዞኑ በሁሉም መዋቅሮች የሚከበር ሲሆን መስከረም 12-13/2018 የብሔሩ ተወላጆች እና የተለያዩ እንግዶች በተገኙበት በሆሣዕና ከተማ በሀዲይ ነፈራ በአደባባይ በደማቅ ሁኔታ እንደሚከበርም አስታውቀዋል።
በዓሉ ሲከበር በሀዲያ እሴትና ባህል ወግ መሰረት በመተሳሰብ እና በመደጋገፍ ማክበር እንደሚገባም ጥሪ አስተላልፈዋል።
የበዓሉ ተሳታፊዎችም በዓሉ የተለያዩ መልካም እሴቶችን የያዘ ልዩ በዓል በመሆኑ ለቀጣይ ትውልድ ሳይደበዝዝ ለማሸጋገር በየአካባቢው መከበሩ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።
ትውልዱም እሴቱን በተገቢው ይዞ ማስቀጠል አለበት ብለዋል።
በዓሉ የያሆዴ ካፕ እግር ኳስ ማጠቃለያ የዋንጫ ጨዋታን ጨምሮ በተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች ታጅቦ በድምቀት ተከብሯል።
ዘጋቢ: ኤርጡሜ ዳንኤል – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት የበለፀገች ሀገር ለመገንባትና አንድነትን ለማጠናከር አጋዥ መሆኑ ተገለፀ
ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) የቦንጋ ከተማን የኮሪደር ልማት ጎበኙ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት ከ2 ሺህ 291 ኪሎ ሜትር በላይ የጠጠር መንገድ እና 112 ድልድዮች ይገነባሉ