ከተስፋ ወደ ሚጨበጥ ብርሀን ለመሻገር በተሰሩ ተግባራት ውጤት ማምጣት መቻሉ ተገለጸ

ከተስፋ ወደ ሚጨበጥ ብርሀን ለመሻገር በተሰሩ ተግባራት ውጤት ማምጣት መቻሉ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ጷጉሜን 2/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከተስፋ ወደ ሚጨበጥ ብርሀን ለመሻገር በተሰሩ ተግባራት ውጤት ማምጣት መቻሉን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አለማየሁ ባውዲ ገለጹ፡፡

‎የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ለአቅመ-ደካማ አናት ያስገነባውን መኖሪያ ቤት አስረከበ፡፡

‎ወ/ሮ ታደለች ካሳ በአርባምንጭ ከተማ ቤሬ እድገት በር ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ የአራት ልጆች እናት ናቸው።

‎ በጉብዝናቸው ወራት ኑሮን ለማሸነፍ ለረዥም አመታት እንጨት በመልቀም ቤተሰባቸውን ሲያስተዳድሩ ቆይተዋል።

‎በበጋው ንፋስ፣ በክረምቱ ቁርና ዝናብ ቤታቸው እያፈሰሰባቸው ተቸግረው የሰው ያለ ሲሉ የቆዩ ሲሆን ሳያስቡ የክልሉ ገቢዎች ቢሮ በወረሀ ታህሳሰ 29 ቀን 2017 ቤታቸውን ሊሰራላቸው ቃል ሲገባ በወቅቱ ደስታቸው በተስፋ እንባ የታጀበ ነበር።

‎ በ’ኅብር ‘ቀን ቃል በተገባላቸው መሠረት አዲስ አመትን በአዲስ ቤትና በብሩህ ተስፋ እንዲያከብሩ የተገነባላቸውን ቤት ቁልፍ አስረክቧቸዋል።

‎በዚህም ደስታቸው አጥፍ ድርብ በሆነ የደስታ እንባ ገልጸዋል።

‎የወ/ሮ ታደለች ጎረቤቶችም አቅመ ደካማነታቸውንና የገቢ አቅም እንደሌላቸው ተገንዝቦ የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ቤታቸውን አስገንብቶ ማስረከቡ ለሁሉም አርአያነት ያለው ተግባር ነው ሲሉ መስክረዋል።

‎የአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ዋና የመንግስት ተጠሪ ወ/ሮ ልሳነ ወረቅ ካሳዬ ፤ እንደ ሀገር የሪፎርም ስራ ከተጀመረ ወዲህ ሰው ተኮር ተግባራት በስፋት እየተከናወኑ መሆናቸውንና በተለይ አቅመ ደካሞችን በማገዝና በመደገፍ ረገድ እንደ ከተማ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመዋል።

‎በከተማዋ ከሚገኙ አቅመ ደካሞች አንዷ ለሆኑትን እናት የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ቤት አስገንብቶ በማስረከቡ ምስጋና አቅርበዋል።

‎የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ አለምነሽ ደመቀ ቤት ለተገነባላቸው እናት የቁልፍ ርክክብ ሲያደርጉ እንደገለጹት የገቢዎች ቢሮ ገቢ ከመሠብሰብ ባለፈ ማህበራዊ ሀላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰዋል።

‎የደከሙና አጋዥ ያጡ አቅመ ደካሞችን በማገዝና በመደገፍ ረገድ እንዲሁም ተመጣጣኝ የኑሮ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ የማድረግ ሀላፊነትን መወጣት ከሁሉም ይጠበቃል ብለዋል።

‎የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አለማየሁ ባውዲ ፤ ከለውጡ ወዲህ በስፋት የሚታየውን የመተባበርና የመተጋገዝ ባህል በማስቀጠል ለአቅመ ደካሞች መድረስ ከሁሉም የሚጠበቅ ተግባር ነው።

‎የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ደረጃውን የጠበቀ ቤት አስገንብቶ ማስረከቡ የሚደነቅ ተግባር ነው ያሉት አቶ አለማየሁ ፤ ለሌሎች ተቋማት ይህንን አርአያነት በሁሉም ዘርፍ ማስቀጠል ያስፈልጋል ብለዋል።

‎”ከተስፋ ወደ ሚጨበጥ ብርሀን “ለመሻገር በተሰሩ ተግባራት ውጤት ማምጣት ጀምረናል በመሆኑም በጎነትን በሁሉም ደረጃ በማስፋት ዜጎች እንዲቀየሩ ሀላፊነት መወጣት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

‎ዘጋቢ ፡ ማርታ ሙሉጌታ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን