ሙስሊሙን ማህበረሰብ ተጠቃሚ በሚያደርጉ ተግባራት ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ አዲስ የተመረጡት የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት አባላት ገለፁ

ሙስሊሙን ማህበረሰብ ተጠቃሚ በሚያደርጉ ተግባራት ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ አዲስ የተመረጡት የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት አባላት ገለፁ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 29/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) አዲስ የተመረጡ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት አባላት ሙስሊሙን ማህበረሰብ ተጠቃሚ በሚያደርጉ ተግባራት ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ አስታወቁ።

የአባላቱ ምርጫ የተከሄደው የነቢዩ መሀመድ የመውሊድ በዓል በሚከበርበት ወቅት በመሆኑ የሳቸውን ፈለግ በመከተል የወከሉትን ማህበረሰብ በትጋት ማገልገል እንደሚገባ ተጠቁሟል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት በቅርቡ ለዞንና ለክልል ምክር ቤቶች ተወካዮችን ለመሰየም ምርጫ መደረጉ ይታወሳል።

ከተመራጮች መካከል አንዱ የሆኑት እና በህዝበ ሙስሊሙ ለክልል ምክር ቤት አባል እንዲሆኑ የተወከሉት ኢማም ግርማ ሙዘይን እንዳሉት አዳዲስ ተመራጮች ህዝበ ሙስሊሙን ተጠቃሚ በሚያደርጉና የነቢዩ መሃመድን አደራ በተከተለ መልኩ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት መዘጋጀት እንደሚገባቸው ገልፀዋል።

የዘንድሮ የመውሊድ በዓል ህዝበ ሙስሊሙ ተወካዮቹን በሰላማዊና ፍትሃዊ ሁኔታ በመረጠበት ማግስት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ያሉት ኢማም ግርማ፥ ለ1ሺህ 500ኛ ጊዜ ለሚከበረው ለነብዩ መሃመድ የልደት በዓል እንኳን አደረሳችሁ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የሀዲያ ዞን እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ሆነው የተመረጡት ዑስታዝ ሱልጣን ዑስማን በበኩላቸው የተጣለባቸውን እስላማዊ አደራ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመው፥ የነብዩ መሐመድን የልደት በዓል ሲናከብር የእርሳቸውን ደግነት፣ ሰው አክባሪነትና መልካም አርአያነት በመከተል ሊሆን ይገባል ብለዋል።

ነብዩ መሐመድ ለተራበ የሚመግቡ፣ የተቸገረን ሁሉ ጠያቂና የመልካም ስብዕና ባለቤት በመሆናቸው ፤ የእርሳቸውን በጎ ባህርይ በመላበስ የወከሉትን ምዕመን መገልገል ይገባል ብለዋል።

በሁሉም አካባቢዎች በዓሉ ሲከበር ለኢትዮጵያ ሠላም ዱአ በማድረግና ለተቸገሩ ወገኖች ሰደቃ በማውጣት መሆን እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል ።

በመጨረሻም እንኳን ለ1ሺህ 500ኛ የነብዩ መሐመድ መውሊድ በዓል በሠላም አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞታቸውን ኡስታዝ ሱልጣን አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ: ሃጀራ ግርማ – ከሆሳዕና ጣቢያችን