የክልሉን የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግርን በመቅረፍ የውሀ ሽፋኑን ለማሳደግ ከተለያዩ ተራድኦ ድርጅቶች ጋር እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

የክልሉን የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግርን በመቅረፍ የውሀ ሽፋኑን ለማሳደግ ከተለያዩ ተራድኦ ድርጅቶች ጋር እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

ይህ የተገለጸው የዋን ዋሽና ኮዋሽ ፕሮግራሞች አፈጻጸም ግምገማና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ የምክክር መድረክ በወራቤ ከተማ በተካሄደበት ወቅት ነው።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ በዚሁ ወቅት፤ ፕሮግራሞቹ የህብረተሰቡን መሠረታዊ ፍላጎቶች ለማሟላትና ጤናማ አካባቢን ለመፍጠር እያገዙ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የዋን ዋሽ ፕሮግራም ሊጠናቀቅ ጥቂት ጊዜ የቀረው በመሆኑ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በተገቢው ጥራትና በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል አቶ አንተነህ።

በፕሮግራሞቹ የተሰሩ ፕሮጀክቶች በዘላቂነት ማህበረሰቡን መጥቀም እንዲችሉ ብልሽት ሲገጥማቸው ጥገና እንዲደረግላቸው መከታተል እንደሚያስፈልግ ያነሱት አቶ አንተነህ፤ ባለድርሻ አካላት የአካባቢውን ተወላጅ ባለሀብቶች በማስተባበር የማስፋፊያ ስራዎች መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በዚህ ወቅት የክልሉ ውሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ኃይሉ እንደገለጹት፤ የአካባቢውን የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ የዋን ዋሽ እና ኮዋሽ ፕሮግራሞች በክልሉ ተግባራዊ እየተደረጉ ነው።

እንድ ሀገር ከረጅም ጊዜ በፊት የተጀመረው የህዳሴ ግድብ ተጠናቆ ንጋት ሰው ሰራሽ ሀይቅን ሰርተን ባጠናቀቅንበትና የምረቃው ዋዜማ ላይ በመሆን ምክክሩን ማድረጋችን ለቀጣይ ተግባር መነሳሳትን እንደሚፈጥር አቶ ዳዊት አንስተዋል።

የዋን ዋሽ ፕሮግራም በክልሉ ውስጥ በሚገኙ ሰባቱም ዞኖች እና በሁለት ልዩ ወረዳዎች በድምሩ በ21 ወረዳዎች ውስጥ እየተተገበረ የሚገኝ ፕሮግራም መሆኑን የገለጹት አቶ ዳዊት፤ በቀጣይም የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በጊዜ በማጠናቀቅ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ አስረድተዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ የዋን ዋሽና ኮዋሽ የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ሲቀርብ በፕሮግራሞቹ የንጹህ መጠጥ ውሀን ተደራሽ በማድረግ፣ የህብረተሰቡን ጤና በተገቢው ለመጠበቅ ግንዛቤ በመስጠት እንዲሁም በትምህርት ተቋማት ላይ የሴቶችን ንጽህና መጠበቂያ ግንባታ በማከናወን ረገድ ጥሩ አፈጻጸም መመዝገቡን በሪፖርቱ ተገልጿል።

የተያዘው በጀት አመት እቅድ ለውይይት ሲቀርብ በዋን ዋሽ ፕሮጀክት ከ740 ሚሊየን ብር በላይ እንዲሁም በኮዋሽ ፕሮግራም ከ115 ሚሊየን ብር በላይ በጀት መያዙ ተገልጿል።

በቀረበው እቅድ ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን በሁለቱም ፕሮግራሞች እየተሰሩ የሚገኙ ፕሮጀክቶች የማህበረሰቡን ችግር እየቀረፉ መሆናቸውን ያነሱት የውይይቱ ተሳታፊዎች፤ ትምህርት ቤቶች ላይ የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ግንባታና የንጹህ መጠጥ ውሀ አቅርቦት መሰረታዊ በመሆናቸው በትኩረት ሊታይ እንደሚገባቸው አስረድተዋል።

በፕሮግራሞቹ ከዚህ ቀደም የተሰሩ ፕሮጀክቶች አሁን ካለው የማህበረሰብ ክፍል ጋር ተመጣጣኝ ባለመሆኑ የማስፋፊያ ስራዎች እንዲሰሩ የጠቆሙት ተሳታፊዎቹ፤ ቁፋሮ ተደርጎ የቆሙ የውሀ ጉድጓዶችን ለማጠናቀቅ ትኩረት እንዲደረግበት አሳስበዋል።

ዘጋቢ፡ ዳዊት ዳበራ – ከወልቂጤ ጣቢያችን