የተሻሻለ የላም ዝሪያ በመጠቀም የወተት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ የጊምቦ ወረዳ አስተዳደር ገለጸ
በወረዳው የይቢጦ እና ሃማኒ ቀበሌዎች የተቀናጀ የሲንክሮናይዜሽን ዘመቻ በይፋ ተጀምሯል፡፡
የጊምቦ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ትብብሩ አሰፋ፤ ዘመኑ የቴክኖሎጂ እንደመሆኑ መጠን እየመጡ ያሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ከጊዜው ጋር አብሮ መጓዝ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
በተለይ የወተት ላሞችን በማዳቀል የወተት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ይገባል ብለዋል፡፡
የላሞችን ቁጥር ከማብዛት ይልቅ ከፍተኛ ወተት የመስጠት አቅም ያላቸው ላሞች ዝሪያ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በጊምቦ ወረዳ ግብርና አካባቢ ጥበቃና ህብረት ሥራ ልማት ጽህፈት ቤት የእንስሳት ዝሪያ ማሻሻል ባለሙያ አቶ መስመሩ ቦጋለ፤ በወረዳው የይቢጦና ሃማኒ ቀበሌዎች ላይ የማዳቀል ሥራ በዘመቻ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
በወረዳው 1 ሺህ 5 መቶ 98 ላሞችን ለማዳቀል የታቀደ ሲሆን ከእነዚህም 1 ሺህ 13 ጥጃዎች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡
በመደበኛ፣ በለይቶ ፆታ ማዳቀል፣ በሲንክሮናይዜሽንና በተሻሻለ ኮርማ የማዳቀል ሥራዎች እንደሚሠሩም ነው አቶ መስመሩ የገለጹት፡፡
በዚህም በአሁኑ ሰዓት በወረዳው በሆርሞን የታገዘ የሲንክሮናይዜሽን ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በካፋ ዞን ግብርና አካባቢ ጥበቃና ህብረት ሥራ ልማት መምሪያ የእንስሳትና አሳ ሃብት ልማት ዘርፍ የዝሪያ ማሻሻል ሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሳልልህ ወንድሙ እንደገለጹት፤ ሲንክሮናይዜሽን በአንድ ጊዜ በርካታ ጥጃዎችን ከማስገኘት ባለፈ ከፍተኛ የወተት ምርት ይሰጣል፡፡
አርሶ አደሮች፤ ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክረ-ሃሳብ ተግባራዊ በማድረግ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ተግባሩ በሁሉም የዞኑ አካባቢዎች እንደሚከናወን የገለጹት አቶ ሳልልህ፤ ዞኑ ይህ ተግባር የተሳካ እንዲሆን ድጋፍ እንደሚያደርግም ነው የተናገሩት፡፡
በክልል ደረጃ 75 ሺህ ላሞችና ጊደሮችን በሰው ሰራሽ የማዳቀል ዘዴ ዝርያን በማሻሻል የወተት ምርትና ምርታማነት ላይ ተጨማሪ ዕድገት ለማስመዝገብ በትኩረት እንደሚሰራ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው መግለፃቸው ይታወሳል፡፡
ዘጋቢ፡ ዳንኤል መኩሪያ – ከቦንጋ ጣቢያችን
More Stories
የክልሉን የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግርን በመቅረፍ የውሀ ሽፋኑን ለማሳደግ ከተለያዩ ተራድኦ ድርጅቶች ጋር እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ
የነብዩ መሐመድ የልደት በዓል ሲከበር የእርሳቸውን አርዓያ በመከተል መልካም ተግባራትን በማከናወን ሊሆን እንደሚገባ ተገለጸ
የነብዩ ሙሐመድ የመውሊድ በዓል ሲከበር ህዝበ ሙስሊሙ ፈለጋቸውን ተከትሎ በእለቱ ከተዘጋጀው ለአቅመ ደካሞች በማካፈል ማክበር እንደሚገባ የይርጋጨፌ ኑር መሰጅድ እማም ሼክ ከድር አደም አስታወቁ