‎የነብዩ ሙሐመድ የመውሊድ በዓል ሲከበር ህዝበ ሙስሊሙ ፈለጋቸውን ተከትሎ በእለቱ ከተዘጋጀው ለአቅመ ደካሞች በማካፈል ማክበር እንደሚገባ የይርጋጨፌ ኑር መሰጅድ እማም ሼክ ከድር አደም አስታወቁ

‎የነብዩ ሙሐመድ የመውሊድ በዓል ሲከበር ህዝበ ሙስሊሙ ፈለጋቸውን ተከትሎ በእለቱ ከተዘጋጀው ለአቅመ ደካሞች በማካፈል ማክበር እንደሚገባ የይርጋጨፌ ኑር መሰጅድ እማም ሼክ ከድር አደም አስታወቁ

‎ነብዩ መሐመድ ለሰው ልጅ አዛኝ እና ርህሩህ ስለነበሩ የእርሳቸውን ባህሪ በመላበስ ወጣቶች የተለያዩ አካላትን የሚመግቡበት ፕሮግራም በነባሩ የይርጋጨፌ ኑር መስጅድ እንደሚከናወን ተገልጿል።

‎ኡስታዝ ከድር አደም መሐመድ በይርጋጨፌ ነባሩ ኑር መስጅድ እማም ናቸው። ነብዩ መሐመድ የዛሬ 1 ሺህ 5 መቶ ዓመት በመካ ሳውዲ አረቢያ ተወልደው ሙሉ ስማቸው ሙሐመድ እብኑ አብዱል ሙጣልብ ሲሆን ሲወለዱ አባታቸው አብዱል ሙጣልብ በሕወይት ስላልነበሩ በአያታቸው እና በአጎታቸው እንክብካቤ ነበር ያደጉት።

‎በእድገታቸው ወቅት በሚሠሩት መልካም እና እውነተኛ ሥራቸው መሐመዱል አምን ወይም ታማኙ እና እውነተኛው መሐመድ የሚለውን ስም ማግኘት ከመቻላቸውም በላይ በሁለት ሰዎች መካከል በሚሰጡት ፍርድም ከእውነተኝነት እና ሀቀኝነት የመነጨ በዳዩም ሆነ ተበዳዩ በፍርዳቸው ተደስተው ይለያዩ እንደነበር የእምነቱ ድርሳናት ያስረዳሉ።

‎እንደ ኡስታዝ ከድር አደም ገለፃ ነብዩ መሐመድ በ40 ዓመታቸው በነብይነት በአላህ ተመርጠው በእስልምና አስተምህሮ ለሰው ልጅ በሙሉ መልካም ተግባር እንዲከውኑ ጥሪ ሲያደርጉ በወቅቱ አረቦች የሴት ልጅን በሕይወት ይቀብሩ የነበሩበትን ሂደትም በማስቀረት ክብር ለሴት ልጅ እንዲሰጥ ከማድረግም ባለፍ የነበሩ የጭቆና፣ ዘረኝነት እና የባርነት መከራዎችን በማስቀረት ባዕድ አምልኮን በማንኮታኮት ለሰው ልጅ መልካም ተግባር በማስተማር የፍትህን ያሰፈኑ ነብይ ናቸው።

‎ከርሳቸው በመማር እና ፈለጋቸውን በመከተል ሙስሊሙ ማህበረሰብ የእርሳቸውን መውሊድ በሚያከብርበት ጊዜ አቅመ ደካሞችን በመርዳት፣ በመመገብ እና በመንከባከብ የእስልምና እምነት የማይከተሉ አቅመደካሞችን ጨምር በእለተ መውሊድ ማስታወስ እና መመገብ ሰደቃ በመሆኑ መፈፀም የሚገባው መልካም ተግባር ነው ብለዋል።

‎አቶ ሰይድ ኢብራሂም እና ሳባህ አለሙ የይርጋጨፌ ኑር መስጅድ አስተዳደር አባላት ናቸው። በይርጋጨፌ ከተማ እና ወረዳ የሚገኙ ሁሉም ሙስሊም ማህበረሰብ ከሌላው ኢድ አል ፈጥር እና ኢድ አል አድኃ በተለየ መልኩ የሚከበር ሲሆን የነብዩ መሐመድ መውሊድ በአንድነት እና በእስላማዊ ወንድማማችነት የሚያከብሩት፣ ማዕድ የሚጋሩበት ከመሆኑም በላይ አቅመደካሞችን ከዘረኝነት እና ከአድሎ በፀዳ መልኩ የሚረዱበት፣ የሚመግቡበትም ነው ሲሉ ‎ተናግረዋል።

‎ሙስሊም ወጣቶች የነብዩን መልካም አስተምሮ በተከተለ መልኩ የሃይማኖቱ ተከታይ ያልሆኑ ወገኖቻችንን ጨምሮ ደካማ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመመገብ እና በመንከባከብ እንደሚያሳልፉ አስረድተዋል።

‎ዘጋቢ፡ አብዶ አያላ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን