በኩታ ገጠም እየተከናወነ ባለው የቡና እና ሌሎች ፍራፍሬ ምርት ተከላ ኢኒሼቲቭ የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት በአጭር ጊዜ እያሳደገ መምጣቱን በሀላባ ዞን የዌራ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ

ባህር ዛፍን ጨምሮ ሌሎች ምርት አልባ ዛፎችን ከለም መሬት በማንሳት በቡና እና በተለያዩ ፍራፍሬ ተክሎች የመተካት ተግባር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጉልህ ሚን እንደሚኖረውም ተጠቁሟል።

በሀላባ ዞን የዌራ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጀማል ሚሓሌ እንደገለፁት፤ በወረዳው የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ተከናውነዋል።

አርሶ አደሮች ያላቸውን መሬት አሟጠው እንዲጠቀሙ በማስቻል የምግብ ሉዓላዊነትን እውን ለማድረግ የቡና እና ሌሎች የፍራፍሬ ተክሎችን በተለያዩ አካባቢዎች በኩታ ገጠም የመትከል ዘመቻ ስራ ሲሰራ መቆየቱን ኃላፊው ገልፀዋል።

በዚህም አነስተኛ የማይባል የለም መሬት ሽፋን ይዞ የነበረውን ባህር ዛፍን ጨምሮ ሌሎች ምርት አልባ ዛፎችን ከለም መሬት በማንሳት በቡና እና በተለያዩ ፍራፍሬ ተክሎች የመተካት ሰፊ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አቶ ጀማል ጠቅሰዋል።

በመሆኑም በወረዳው በሚገኙ ቀበሌያት በጥቅሉ ከ25 ሄክታር መሬት በላይ በባህር ዛፍ ተሸፍኖ የነበረ መሬት በቡና ተክል የመተካት ውጤታማ ሥራ መሠራቱን ኃላፊው አክለዋል።

የሙዝ፣ ፓፓያ፣ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ የእንሰትና ሌሎች ዘርፈ ብዙ የፍራፍሬ ተክሎችን በሥፋት በመትከል የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ተግባር እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል::

የቡና ተክልን ጨምሮ ሌሎች ለምግብነት የሚውሉ ፍራፍሬዎችን ሙሉ በሙሉ የግብርና ጽ/ቤቱ እያቀረበላቸው መሆኑንም አብራርተዋል።

በዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ ተስፋ ሰጪ እና አበረታች ውጤት እየታየ መሆኑንም አብራርተዋል::

ከተረጂነት ለመላቀቅ ሁሉም ማህበረሰብ የበኩሉን ድርሻ ከተወጣ የምግብ ሉዓላዊነት በአጭር ጊዜ እንደሚረጋገጥ አመላክተዋል::

በወረዳው ያነጋገርናቸው ሞዴል አርሶ አደሮች በበኩላቸው በተመቻቸላቸው የቡናና የፍራፍሬ የኩታ ገጠም ተከላ መርሃ ግብር ትግበራ ከወዲሁ ተጠቃሚነታቸው እየጎለበተ መምጣቱን ተናግረዋል::

ዘጋቢ: አብዱልሰመድ አወል – ከሆሳዕና ጣቢያችን