የፈጠራ ችሎታ ያላቸው ተማሪዎችና መምህራንን በመደገፍ የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታት በትኩረት እየሠራ መሆኑ ተገለጸ

የፈጠራ ችሎታ ያላቸው ተማሪዎችና መምህራንን በመደገፍ የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታት በትኩረት እየሠራ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 27/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የፈጠራ ችሎታ ያላቸው ተማሪዎችንና መምህራንን በመደገፍ የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታት በትኩረት እየሠራ መሆኑን የደቡብ ኦሞ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው አዘጋጅነት የተማሪዎችን ሳይንስና ፈጠራ ሥራዎችን ለማሳደግ የሚያግዝ አወደ ርዕይ በዲመካ ከተማ ተካሂዷል።

በኤግዝብሽኑ የፈጠራ ሥራቸውን ያቀረቡ ተማሪዎች፥ የሳይንስ ንድፈ ሀሳቦችን በአከባቢያቸው የሚገኙ የተለያዩ ዕቃዎችን በመጠቀም በማህበረሰቡ ዘንድ የሚስተዋሉ ችግሮችን ሊቀርፉ የሚችሉ የፈጠራ ሥራዎችን ማቅረባቸውን ተናግረዋል።

በአውደ ርዕይ ከተሳተፉ መካከል የበናፀማይ እና የሐመር ወረዳ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ፅ/ት ቤት የፈጠራ ሥራ ባለሙያ የሆኑት ወ/ሮ ባዩሽ ጌታቸውና ማንአለብሽ አሰፋ በጋራ እንደገለፁት በትምህርት ቤቶች የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታት የሚያግዙ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ አስፈላጊውን ድጋፍ ለተማሪዎች እንደሚያደርጉ አስረድተዋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ ወ/ት ብሩክታዊት አኮ በበኩላቸው፥ የሳይንስና ፈጠራ ሥራዎችን ለማሳደግ ከትምህርት ቤቶች ጋር በመቀናጀት የሳይንስ ሣምንትን በየደረጃው በማክበር ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራ ላቀረቡ ተማሪዎች የዕውቅናና የግብዓት ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የውሃ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ታደለ ጋያ፥ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን ለማሳደግና ዘርፉን ለማጠናከር በዞኑ ከሚገኙ የቴክንክና ሙያ ኮሌጆች ጋር በመተባባር ብቁ ዜጋ ለማፍራት ይሠራል ብለዋል።

በሳይንስና ፈጠራ ሥራዎች ተሳትፈው የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ አካላት የተለያዩ ሽልማቶች ተበርክቶላቸዋል።

ዘጋቢ፡ ተመስገን አሰፋ – ከጂንካ ጣቢያችን