የክልሉን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ የሚችል የፖሊስ መዋቅር መፍጠር እንደሚገባ ተገለጸ

የክልሉን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ የሚችል የፖሊስ መዋቅር መፍጠር እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 27/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የክልሉን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ የሚችል የፖሊስ መዋቅር መፍጠር እንደሚገባ ተገለጸ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አሳሰበ።

ቢሮው በ2017 በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸሙን በቦንጋ ከተማ እየገመገመ ነው።

የፖሊስ መዋቅሩን ጠንካራ ተግባራት ማስቀጠልና ድክመቶችን ማስተካከል አስፈላጊ መሆኑን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ ገልጸዋል።

የክልሉን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ የሚችል የፖሊስ መዋቅር መፍጠር የግምገማ መድረኩ አላማ መሆኑን አቶ አንድነት ጠቁመው፥ የክልሉ አጠቃላይ የፖሊስ አባላትና አመራሮች የተለያዩ የማኔጅመንት አካላት በተገኙበት እየተገመገሙ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ በትራንስፖርት ዘርፍ ከታሪፍ በላይ ማስከፈል፣ ከመጠን በላይ መጫንና መሰል ችግሮች እንዲቀረፉ የፖሊስ አባላትን ሚና በአግባቡ መፈተሽና ተጠያቂነትን ማስፈን አስፈላጊ መሆኑን አመላክተዋል።

በኮንትሮባንድና ህገ-ወጥ የንግድ ቁጥጥር ስራዎች ላይ የሚስተዋሉ እንቅስቃሴዎችን መፈተሽ ሌላኛው የመድረኩ አላማ መሆኑን አቶ አንድነት ገልጸው፥ ወንጀልን አስቀድሞ ከመከላከል አንጻር መረጃ ላይ የተመረኮዘ ስራ እንዲኖር “የፖሊስ መዋቅሩ እንዴት መራው?” የሚሉ ጉዮችን መፈተሽ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመከላከል በየደረጃው የሚገኙ የፖሊስ አባላትንና የአመራሩን ሚና በመገምገም የመፍትሄ አቅጣጫ ማስቀመጥ ያስፈልጋል ብለዋል።

መሰል የግምገማ መድረክ በሁሉም ዞኖች፣ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚቀጥል መሆኑን የገለጹት አቶ አንድነት ፤ አባላቱ ህዝብን የማገልገል ተግባራትን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

3 ሺ 987 የፖሊስ አባላትና አመራሮች የሚገመገሙ ሲሆን ፤ ከእነኚህም ውስጥ 857ቱ በክልል ደረጃ ይገመገማሉ ብለዋል።

በግምገማው መድረክ በምክትል ርዕሰ-መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ-ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ፋጅዮ ሳፒን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የፖሊስ መኮንኖችና አባላት ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡ ትዕግስቱ ጴጥሮስ – ከቦንጋ ጣቢያችን