የዲሜ ልማት ማህበር ከራሱ ባለፈ ሌሎችንም የሚያግዝ ማህበር እንዲሆን ግንባር ቀደም ሆኖ መስራት ያሰፈልጋል ሲል የደቡብ ኦሞ ዞን ብልጽግና ፖርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ገለፀ

የዲሜ ልማት ማህበር ከራሱ ባለፈ ሌሎችንም የሚያግዝ ማህበር እንዲሆን ግንባር ቀደም ሆኖ መስራት ያሰፈልጋል ሲል የደቡብ ኦሞ ዞን ብልጽግና ፖርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ገለፀ

‎የዲሜ ልማት ማህበር 4ኛ ዓመት ምስረታ በዓል እና 2ኛ ዙር የማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ በወይዴ ቀበሌ ተካሂዷል።

‎ጉባኤው በሀይማኖት አባቶች እና በባህል መሪዎች ምርቃትና ፀሎት ነው የተጀመረው።

‎የሳላማጎ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ህጉ ቅጣቱ በጉባኤው መክፈቻ ንግግራቸው፤ ማህበሩ በርካታ ፈተናዎችን አልፎ አራት አመታትን በጅምር ሥራዎች ቆይቶ ለዚህ በመብቃቱ መደሰታቸውንና ለዚህ ያበቁ አካላትን አመስግነው፤ ከልዩነት ይልቅ አለመግባባቶችን በውይይት በመፍታት አንድነትንና አብሮነትን ልናጠናክር ይገባል ብለዋል።

‎አክለውም እንደ አካባቢ ብሎም እንደሀገር አስተሳሳሪ ትርክት እንዲገነባ መንግስት እየሰራ ያለውን ሥራ ህዝቡ በማገዝ በንቅናቄ ያሳየውን አጋርነት በማህበሩም ውጤታማነት ላይ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ አሳስበዋል።

‎የደቡብ ኦሞ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪና የብልጽግና ፖርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊና የዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ ታደሰ ጋልጶክ፤ ማህበሩ እዚህ እንዲደርስ አስተዋጽኦ ያደረጉ አመራርና አባላትን አመስግነው የማህበሩ አላማ አንድነትን በማጉላት የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን በማጠናከር ሁሉንም ያቀፈ ሰብዓዊነትን ያስቀደመ ተግባር በማከናወን የመንግስት ክፍተትን ማገዝ ነው ብለዋል።

‎በዚህም ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ከማህበር በላይ ከፍ አድርጎ በማየት ጠንካራ ሆኖ ከራሱ ባለፈ ሌሎችንም የሚያግዝ ማህበር እንዲሆን ግንባር ቀደም ሆኖ በመስራት በቀጣይ የተለያዩ ሚዲያዎችን በመጋበዝ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦችን ያሳተፈ ጉባኤና በዓል በማካሄድ የብሔረሰቡን ቱባ ባህሎች፣ እሴቶችና ሌሎች የልማት ትርፋቶችን ለማስተዋወቅ ይሰራል ተብሏል።

‎የውይይት መነሻ ሰነድ የቀረበ ሲሆን ከተሳታፊዎችም የዲሜ ብሔረሰብ አዲሰ ዓመት አከባበር፣ የማህበሩ ስያሜ የብሔረሰቡ ኪነት ቡድን አባላት ማቋቋም የአባላት መዋጮ እና ሌሎችም ጥያቄና አስተያየቶች ተነስተው ተገቢ መሆኑን በማመን የጠቅላላ ጉባኤው አመራርና የመድረኩ መሪ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

‎በመጨረሻም ማህበሩን ከዚህ ቀደም ያገለገሉትን በመሸኘት አምስት አባላት ያሉት አዲስ የማህበሩ አመራር አባላት በመምረጥ በስኬት ተጠናቋል።

‎ዘጋቢ: ከተማ በየነ – ከጂንካ ጣቢያችን