በካፋ ዞን ጨና ወረዳ በምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም (FSRP) የተከናወኑ የልማት ስራዎች ላይ ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ጋር የልምድ ልውውጥ ተደረገ

የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተረፈ ገብረማርያም እንደገለጹት፤ ፕሮግራሙ በወረዳው የሚገኙ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደረጉ ተግባራትን እያከናወነ ነው።

ከ26 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ጪታ እና ዳዊ ድልድዮች በዚህ ፕሮጀክት የተገነቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በፕሮግራሙ ድጋፍ አለዋ ኦፊያ እና ቀኔች መስኖ አውታሮች መገንባታቸውን ያነሱት ዋና አስተዳዳሪው ይህም አርሶ አደሩ ከዝናብ ጠባቂነት እንዲላቀቅ ረድቶታል ብለዋል።

መስኖ ፕሮጀክቶቹ እያንዳንዳቸው ከ100 ሄክታር በላይ መሬት የማልማት አቅም እንዳላቸውም ጠቁመዋል።

የዓሳ ምርታማነትን በወረዳው ለማላመድ የተገነቡ 4 የዓሳ ፖንዶችም የጉብኝቱ አካል ነበሩ።

ፖንዶቹ ለዘር ብዜት እና ለምግብ የሚሆኑ ዓሳዎች የሚመረቱበት ሲሆን በ2018 ምርት በጀት ዓመት ወደ ምርት እንደሚገቡ ጠቅሰዋል።

በሌማት ትሩፋት ትግበራ ላይ ፕሮጀክቱ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸው፤ የተሻሻሉ የቦንጋ በግ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ የማድረግ ተግባር እየተከናወነ ነው።

በተመሳሳይም ከቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የወተት ምርትን ለማሻሻል የተደረገው ጥረት አበረታች መሆኑን ለጉብኝቱ ተሳታፊዎች አብራርተዋል።

አቶ ክፍሌ አምበሴ እና አቶ ገብሬ ዱሻ የኮዳ ቀበሌ አርሶ አደሮች ሲሆኑ በፕሮግራሙ ድጋፍ የተሻሻለ የቦንጋ በግ ዝርያ በማርባት ተጠቃሚ በመሆን ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለአብነት አንድ 5 ወር የሞላው የቦንጋ በግ ሙክት ከ21 ሺ ብር ጀምሮ እንደሚሸጥ ተናግረዋል።

በቀጣይ በዚሁ እርባታ ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን እንደሚሰሩ ለጎብኝዎች አስረድተዋል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ የምግብ ስርዓት ማሻሻያ ፕሮግራም ለድሬዳዋ ከተማ የሚያደርገው የልምድ ልውውጥ በካፋ እና በቤንች ሸኮ ዞኖች ቀጥሏል።

ዘጋቢ፡ ድንቃየሁ ዮሐንስ – ከቦንጋ ጣቢያችን