ሳታ ቴክኖሎጂ እና ቢዝነስ ኮሌጅ በአርባ ምንጭ ካምፓስ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በመጀመሪያ ዲግሪ እና ቴክኒክና ሙያ ስልጠና መስኮች ያሰለጠናቸውን 2 ሺህ 132 ተማሪዎችን አስመረቀ

በምረቃ ስነ ስርዓት ላይ የኮሌጁ ፕሬዝዳንት አቶ አለማየሁ ካሳ እንዳሉት ኮሌጁ ባለፉት 14 ዓመታት በተለያዩ መስኮች በአጫጭር እና ቴክኒክና ሙያ እንዲሁም በዲግሪ እና በማስተርስ ዲግሪ ተማሪዎችን አሰልጥኖ አስመርቋል።

ኮሌጁ ከመምር ማስተማር ጎን ለጎን የሸማ ፓርክን ጨምሮ 10 የቢዝነስ ድርጅቶችን በመክፈት ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉንም አቶ አለማየሁ ካሳ ገልጸዋል።

የዕለቱ ክብር እንግዳ እና የጋሞ ዞን ትምህርት መምሪያ ሀላፊ አዲሱ አዳሙ (ዶ/ር) እንዳሉት ትምህርት ለአንድ አገር የሚኖረው ፋይዳ የላቀ በመሆኑ የግልም ሆነ መንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተለይም የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ   በትኩረት መሥራት ይጠበቅባቸዋል።

ተመራቂዎች የሥራ ፈጣሪ ሆነው ለአገሪቱ ዕድገት የበኩላቸውን እንዲወጡ የመምሪያው ሀላፊ ጥሪ አቅርበዋል።

በኮሌጁ ቆይታቸው የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ተመራቂዎች መዳሊያና ዋንጫ ተሸልመዋል።

ዘጋቢ: ወ/ገብርኤል ላቀው ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን