የፖሊስ አባላትና ሲቪል ሠራተኞች የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበር ጠቅላላ ጉባኤውን አካሄደ

የፖሊስ አባላትና ሲቪል ሠራተኞች የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበር ጠቅላላ ጉባኤውን አካሄደ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 22/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የፖሊስ አባላትና ሲቪል ሠራተኞች የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበር ጠቅላላ ጉባኤ መድረክ አካሄደ።

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰብስቤ ሻዎኖ በግል ሆነ በሀገር ደረጃ ለማደግ ቁጠባ መሰረታዊ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል ብለዋል።

ኮሚሽነሩ አክለውም የፖሊስ አባላት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ከሚያገኙት በመቆጠብና ገቢን በማሳደግ የኑሮ ደረጃቸውን ለማሻሻል በማሰብ ማህበሩ መቋቋሙን ተናግረዋል።

የስራ ሪፖርት ያቀረቡት የማህበሩ ሰብሳቢ ረዳት ኮሚሽነር አለሙ ዳሾ ማህበሩ 81 አባላትን ይዞ በ41 ሺ 300 ብር ካፒታል ከመጋቢት 9/2014 ዓመተ ምህረት መቋቋሙን አስታውሰው፥ በእስካሁኑ ቆይታ ብዙ ፈተናዎችን በማለፍ ለዚህ መድረሱ አስረድተዋል።

በቀጣይ ማህበሩ የፖሊስ አባላትና ሲቪል ሠራተኞችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚታዩ ክፍተቶችን በማረም እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በመድረኩ ማህበሩ ስራ ከጀመረበት አንስቶ እስካሁን ያለው የኦዲት ሪፖርት በካፋ ዞን ግብርና፣ አከባቢ ጥበቃና ህብረት ሥራ መምሪያ የማህበራት ኦዲተር በአቶ አቤል ወልቀሳ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

ከማህበሩ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ከሚመለከታቸው አካላት ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶበታል።

በቀጣይ ስራዎችን ለማሳለጥና የሚታዩ ክፍተቶችን ለማረም የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴዎችን በመምረጥ ጉባኤው ተጠናቋል።

ዘጋቢ፡ በወይኒቱ ወዳጆ – ከቦንጋ ጣቢያችን