ስራ አጥነትን ደረጃ በደረጃ ለመቀነስና ምርታማነትን ከፍ ለማድረግ የባለድርሻ ተቋማት የተቀናጀ ርብርብ እንደሚሻ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ገለጸ

ስራ አጥነትን ደረጃ በደረጃ ለመቀነስና ምርታማነትን ከፍ ለማድረግ የባለድርሻ ተቋማት የተቀናጀ ርብርብ እንደሚሻ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ገለጸ

ሐዋሳ፣ ነሐሴ 22/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ስራ አጥነትን ደረጃ በደረጃ ለመቀነስና ምርታማነትን ከፍ ለማድረግ የባለድርሻ ተቋማት የተቀናጀ ርብርብ እንደሚሻ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ ገለፁ፡፡

የክልሉ ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ከክልል እንዲሁም ከዞንና ልዩ ወረዳ ከተወጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር በ2017 አፈፃፀምና በ2018 ዕቅድ ላይ የምክክር መድረክ አካሂዷል።

በመድረኩ የተገኙት የቢሮው ኃላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ስራ አጥነትን ደረጃ በደረጃ ለመቀነስና ምርታማነትን ለማሳደግ በክልሉ በየደረጃው የሚገኘውን እምቅ አካባቢያዊ ሀብቶችንና ፀጋዎችን መለየት ቅድሚያ ተሰጥቶ ሊሰራ ይገባል።

ቢሮው በበጀት ዓመቱ ለክህሎት መር ስራ ዕድል ፈጠራ ትኩረት ሰጥቶ ባከናወነው ተግባር ዘላቂና አስተማማኝ ስራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር ኢንተርፕራይዞችን በማደራጀት ምርታማነትና ተወዳዳሪነትን ማጎልበት ላይ ትኩረት በመደረጉ ዜጎች በልቶ ከማደር የተሻገረ ሀብት መፍጠር ላይ እንዲያተኩሩ እና ለሀገር እኮኖሚያዊ እድገት አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጠንካራ ድጋፍ መደረጉንም አቶ ሙስጠፋ አመላክተዋል።

በክልሉ በ2017 በጀት ዓመት በጠንካራ ቅንጅት ድጋፍና ክትትል በመታገዝ ለ3መቶ 71ሺ 3መቶ 55 ስራ ፈላጊ ዜጎች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን የቢሮው ኃላፊ አቶ ሙስጠፋ ጠቁመዋል።

በዘርፉ በግብዓት፣ በክህሎትና በአመለካከት የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በመቅረፍ ረገድ ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን የተናገሩት ኃላፊው በየዓመቱ ከሚፈጠረው የስራ ፈላጊና እየተፈጠረ ያለው የስራ እድል የተመጣጠነ ባለመሆኑ ባለድርሻ አካላት በጉዳዩ ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ አቶ ሙስጠፋ አሳስበዋል።

ቢሮው በ2018 በጀት ዓመት ለክህሎት መር ስራ ዕድል ፈጠራ ትኩረት በመስጠት 4መቶ 81ሺ 7መቶ 88 ስራ ፈላጊዎችን በመለየት ለ4መቶ ሺ ወጣቶች ስራ ዕድል ለመፍጠር ግብ ተጥሎ እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የምክክር መድረኩ በስራ ዕድል ፈጠራና በኢንተርፕራይዝ ልማት ዘርፍ በከተማና በገጠር የሚስተዋሉ ማነቆዎችን በቅንጅት ለመፍታት አጋዥ መሆኑን ገልፀው የወጣቱን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማጎልበት በመሠረተ ልማትና በፋይናንስ አቅርቦት ረገድ ባለድርሻ ተቋማት የድርሻቸውን እንዲወጡ አቋም የተወሰደበት መድረክ ስለመሆኑንም ጠቁመዋል።

የምክክር መድረኩ ቢሮው ከባለድርሻ ተቋማት ጋር የ2018 በጀት ዓመት የግብ ስምምነት ተፈራርመዋል።

ዘጋቢ:- ጡሚሶ ዳንኤል ከሆሳዕና ጣቢያችን