ሀገራችን ኢትዮጵያ የበርካታ ባህላዊ እና ሐይማኖታዊ ይዘትና ዕሴት ያሏቸው በዓላት መገኛ ናት !
ከእነዚህም በዓላት መካከል በወረሃ ነሐሴ 13 የሚከበረው ቡሄ ወይንም የደብረታቦር በዓል ይጠቀሳል።
በዓሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከሚከበሩ ዓቢይ 9 በዓላት መካከል አንዱና በተለያዩ መንፈሳዊ ክዋኔዎች እንደሚከበር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሀዲያና ስልጤ ሀገረስብከት የሆሳዕና ደብረምህረት ወ ደብረታቦር ቅዱስ ባለወልድ ወቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ ሊቀ ሂሩያን ቀሲስ አብርሃም ሞገስ ይናገራሉ።
የቡሄ ወይንም የደብረታቦር በዓል ሐይማኖታዊ መነሻው በቅዱስ መጽሐፍ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ከ17 ጀምሮ ኢየሱስ ክርስቶስ በስጋ ከተገለጠ በኃላ ያደረገውን ጉዞ የሚያመለክት፣ ደቀመዛሙርትን ይዞ ወደ ተራራ የወጣበት፣ እንደ ብርሃን ያንፀባረቀበት፣ ብርሃነ-መለኮቱን የገለጠበት መሆኑን መምህር ሊቀ ሂሩያን ቀሲስ አብርሃም አብራርተዋል።
ተራራው ግርማ መለኮቱን ሲገልጥ ሰዎች ደስ ይላቸዋል በተባለው ትንቢት መሰረት በርካታ ድንቅና ታዓምራት ስለመታየቱ አንስተዋል።
“ቡሄ” ማለት በራ፣ ገለጠ የሚል አቻ ትርጉም ያለው ሲሆን ብርሃነ መለኮቱ የተገለጠበት “የምወደው ልጄ እርሱ ነው፤ እርሱን ስሙት” የሚል ድምጽ ከሰማይ የመጣበት ጠለቅ ያለ ሐይማኖታዊ ትርጉም ያለው ስለመሆኑም አስረድተዋል።
በዓሉ ሐይማኖታዊና ባህላዊ ይዘት ያለው በመሆኑ በበርካታ ክዋኔዎች ታጅቦ እንደሚከበር ያወሱት የሐይማኖት መምህሩ ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን ሲገልጥ የነበረውን ብርሃን ለማስታወስ በደብረ ታቦር ዕለት ማለትም በነሐሴ 13 አመሻሽ ችቦ እንደሚለኮስ፣ በነጎድጓዳማ ድምፅ ብርሃነ መለኮቱን ለማስታወስ ጅራፍ እንደሚጮኽ ይገልጻሉ።
በሀገራችን የቡሄ በዓል በነሐሴ አጋማሽ መዳረሻ የሚከበር ሲሆን “ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት” እንዲሉ አበው፥ ጭጋጋማው የክረምት ወቅት እያለፈ ስለመምጣቱ ማብሰሪያ፣ የወንዞች ሙላት የሚቀንስበት ወደ አዲሱ ዓመት መሻገሪያ ተደርጎ እንደሚወሰድ ጠቁመዋል።
በዓሉን ህፃናትና ታዳጊ ልጆች የማያቁትን ቤት ጭምር እየዞሩ የሚጫወቱበት፣ እናቶች ባዘጋጁት የሙልሙል ዳቦ የሚደሰቱበት በጋራ ኢትዮጵያዊ አንድነት የሚቋደሱበት ስለመሆኑ አብራርተዋል።
ሙልሙል የሚዘጋጀውም በደብረ ታቦር ተራራ አቅራቢያ እረኞች ሕፃናት በብርሃነ መለኮቱ አማካይነት ቀኑ መምሸቱን ረስተው ሲቆዩባቸው እናቶች የሚበላ ሙልሙል ይዘውላቸው የሄዱበትን አብነት በማድረግ እንደሆነም አመላክተዋል።
በዓሉ ሐይማኖታዊ እና የጥንት ባህላዊ ዕሴቱን በጠበቀ መልኩ ለማክበር ቤተክርስቲያን እየሰራች ትገኛለች ያሉት ሊቀ ሂሩያን ቀሲስ አብርሃም፥ ቤተክርስቲያን ላይ ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን በማሰናዳት በድምቀት ተከብሮ እንደሚውል ጠቁመዋል ።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አንዳንድ ሀይማኖታዊና ባህላዊ ይዘቱን ፈር የመልቀቅ ሁነቶች እየታዩ በመሆኑ ህፃናትንና ልጆችን ማስተማር፣ መምከርና መንፈሳዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ ለመጪው ትውልድ በማስተላለፍ ለጋራ አንድነታችን መጠቀም እንደሚገባ የሐይማኖት መምህሩ ምክራቸውን ለግሰዋል።
ዘጋቢ፡ ሄኖስ ካሳ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
በደቡብ ኦሞ ዞን ማሌ ወረዳ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሀ-ግብር ቤት የተገነባላቸዉ አካላት መደሰታቸውን ገለፁ
ሁሉ አቀፍ ድጋፍ የሚሹ አካላትን መርዳት የጥቂት አካላት ተግባር ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሥራ ሊሆን እንደሚገባ ተገለፀ
በደቡብ ኦሞ ዞን ሳላማጎ ወረዳ የአንድ ጀምበር የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተካሄደ