የጉራጊኛ ቋንቋ ይበልጥ እንዲለማና በስራ ላይ እንዲውል የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተገለጸ

የጉራጊኛ ቋንቋ ይበልጥ እንዲለማና በስራ ላይ እንዲውል የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 29/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የጉራጊኛ ቋንቋ ይበልጥ እንዲለማና በስራ ላይ እንዲውል የዞኑ አስተዳደርና ህዝቡ እያደረገው ያለው ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የጉራጌ ዞን አስተዳደር አሳሰበ።

የዞኑ ትምህርት መምሪያ የ3ኛ ክፍል የጉራጊኛ ቋንቋ ትምህርት የሙከራ ትግበራ የመፅሃፍት ዝግጅት ግምገማ በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።

የጉራጌ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የጉራጊኛ ቋንቋ ልማት የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ፈቀደ እንደገለፁት የጉራጊኛ ቋንቋ የትምህርት የስራና የሚዲያ ቋንቋ እንዲሆን ለማስቻል ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው በሰሩት ስራ ዉጤት እየተመዘገበ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የጉራጊኛ ቋንቋ በትምህርት እና በየሚዲያ መዋሉ ቋንቋውን ይበልጥ እንዲለማ ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖረው አቶ ደሳለኝ ጠቁመው፥ በአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት አሰጣጥ ተግባር ላይ የሚታዩ ጉድለቶች ደረጃ በደረጃ እንዲፈቱ ጥረት ይደረጋል ነው ያሉት ።

የጉራጊኛ ቋንቋ ይበልጥ እንዲለማና በስራ እንዲውል የዞኑ አስተዳደርና ህዝቡ እያደረገው ያለው ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አቶ ደሳለኝ አሳስበዋል።

የዞኑ ትምህርት መምሪያ ሃላፊ አቶ መብራቴ ወልደማርያም በበኩላቸው አንድ ቋንቋ የባህል፣ የማንነት መገለጫ መሆኑን አንስተው የጉራጊኛ ቋንቋ በትምህርት ስርአት ውስጥ ቀርፆ ስራ ላይ ለማዋል ባለድርሻ አካላት እያደረጉት ያለውን ተሳትፎ አመስግነው በቀጣይም ተግባሩ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመላክተዋል።

በአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት የመስጠት ትግበራ የትምህርት አሰጣጥና የግብአት አቅርቦት በተመለከተ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጦች እንዳሉም ሃላፊው ተናግረው፥ የመማር ማስተማር ሂደቱን በማሻሻል ህፃናት ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ ለ191 መምህራን የአቅም ግንባታ ስልጠና እንደሚሰጥ አንስተዋል።

በዞኑ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ህፃናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ትምህርት የመስጠት ጉዳይ ተግባራዊ ቢሆንም በአንዳንድ አካባቢዎች ክፍተቶች እንዳሉ ጠቁመው ስለሆነም በቋንቋው የሰለጠ መምህራን የማፍራትና ሌሎችም መሰል ጉድለቶች በመለየት ሁሉም ባለድርሻ አካል በቀጠይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚጠበቅበት አመላክተዋል።

የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ መሠረት አመርጋ የጉራጊኛ ቋንቋ የስራ፣ የትምህርትና የሚዲያ ቋንቋ እንዲሆን ለማስቻል ከፍትህ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ የአስራር መመሪያና ደንቦች እንዲዘጋጁ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

አክለውም መመሪያው ክልሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየሰራው ያለው ስራ ውጤታማ እንዲሆን ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ገልፀዋል።

የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት በሰጡት አስተያየት የተጀመረው የቋንቋ ልማት ስራ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን የሚያጋጥሙ ችግሮች ሊፈቱ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በመጨረሻም የመፅሃፍት ህትመቱ በቁርጠኝነትና በመተጋገዝ የተዘጋጀ መሆኑ አንስተው በቀጣይም የተጀመሩ ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡ እርካብነሽ ወልደማርቆስ – ከወልቂጤ ጣቢያችን