በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል “በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ ሃሳብ የተጀመረው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በሃላባ ዞን ዌራ ወረዳ ታች በደኔ ቀበሌ ላይ ተካሄደ
ሀዋሳ: ሐምሌ 24/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በክልሉ የሚካሄደውን የችግኝ ተከላ በስፍራው ተገኝተው ያስጀመሩት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር እንዳሻው ጣሰው፥ ባለፉት ሰባት አመታት በተከታታይ በተደረገ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ውጤት መመዝገቡን ጠቁመው፥ በዘንድሮ የችግኝ ተከላ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እየተመዘገበ ላለው ውጤት ዘላቂነት እንዲኖረው የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጠይቀዋል።
እንደ ሀገር በተጀመረው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በ2011 በአንድ ሰው 40 ችግኝ፣ በ2012 በአለም አቀፍ ደረጃ ተከስቶ የነበረውን የኮረና ወረርሽኝ እየተጠነቀቅን እንተክላለን በሚል መሪ ቃል የችግኝ ተከላው መካሄዱን ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በ2013 ኢትዮጵያን እናልብሳት፣በ2014 አሻራችንን ለትውልዳችን፣በ2015 ነገን ዛሬ እንትከል ፣በ2016 የምትተክል ሀገር የሚያጸና ትውልድ፣ ዘንድሮ ደግሞ በመትከል ማንሰራራት በሚል መሪ ሀሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ700 ሚሊየን በላይ ችግኞች በአንድ ጀንበር የመትከል ዘመቻ እየተካሔደ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ በአንድ ጀንበር ከ6 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ችግኞች እየተተከሉ ስለመሆኑ ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመው፥ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ያስመዘገብናቸው ውጤቶች ከፍተኛ ናቸው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተስፋ ብርሐን ወደሚጨበጥ ብርሐን የምንሸጋገርበት ነው ብለዋል።
በ2023 ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ የብልጽግና ተምሳሌት አብነት እንድትሆን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመው፥ በ2040 ደግሞ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በአለም አቀፍ ደረጃ የብልጽግና አርአያ እንድትሆን ዘርፈ ብዙ ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን አስረድተዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ስሩር በኩላቸውአረንጓዴ አሻራ ለአለም አቀፍ ችግር ኢትዮጵያዊ ዘላቂ መፍትሄ መሆኑን ገልፀው፥ ባለፉት 7 አመታት በተሰሩ ስራዎች የተመዘገቡ ውጤቶች ለምርታማነት እድገት እና ለህዝብ ተጠቃሚነት ከፍተኛ ድርሻ ማበርከቱን ተናግረዋል።
የተራሮች አረንጓዴ መልበስ፣ የደን ሽፋን ማደግ፣ የግድቦች፣ ወንዞችና ሀይቆች ከደለል ሙላት መዳን፣ የምርታማነት መጨመር፣ የመስኖ አቅም ማደግ፣ የፍራፍሬ፣ የቡና ሽፋን ማደግ፣ የእንስሳት መኖ፣ የምርት ማደግ፣ የስራ ባህል ለውጥ፣ ለወጣቶች የስራ እድል መፈጠር፣ የአካባቢዎች ገፅታ መቀየር፣ የህብረተሰቡ የባለቤትነት ስሜት ማደግ፣ ከዘመቻነት ወደ ባህል እያደገ መምጣቱን ገልፀዋል።
በተከላውም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ትኩረት እንደተሰጣቸው ጠቅሰው፤ ከሚተከሉ ችግኞች ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው መሆኑን ጠቁመው፥ ለምግብነት የሚውሉ፣ የመሬት ለምነትንና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ያስችላል ብለዋል።
እንደ ክልል ከ500 ሚሊዮን በላይ ችግኝ እንደሚተከል የገለፁት አቶ ኡስማን 310 ሚሊዮን ችግኝ የፍራፍሬ፣ የቡና፣ የዕንሰት እና የጥምር ደን መሆኑን ገልፀው፥ 190 ሚሊየን ደግሞ ለዓላማ ተኮር ጥቅም የሚሰጡ የደን ውጤቶች እንደሚተከሉ አስረድተዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የክልሉ የስራ ኃላፊዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች፣ የሴቶች አደረጃጀቶችና ሁሉም ባለድርሻ አካላት በችግኝ ተከላው ላይ እየተሳተፉ ነው።
ዘጋቢ፡ ዘላለም ተስፋዬ
More Stories
”የምንተክላቸው ችግኞች ለትውልድ ተሻጋሪ ትሩፋትን የሚያስገኙ ናቸው” – ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ
ከማረምና ማነጽ ጎን ለጎን የሀገሪቱን አረንጓዴ ልማት እስትራቴጂን ለማሳካት ሚናውን እንደሚወጣ የጂንካ ማረሚያ ተቋም አስታወቀ
“በክልሉ ባለፉት አመታት የተተከሉ ችግኞች ለኢኮኖሚ እና የስራ ዕድል ፈጠራ ምንጭ ሆነዋል” ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ