የCRFL ፕሮጀክት ያለፉት አምስት ዓመታት አፈጻጸም በቦንጋ ከተማ እየተገመገመ ነው

የCRFL ፕሮጀክት ያለፉት አምስት ዓመታት አፈጻጸም በቦንጋ ከተማ እየተገመገመ ነው

መድረኩ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ካፋ ዞን ላለፉት 5 ዓመታት በፕሮጀክቱ የተከናወኑ ተግባራት ተገምግመው የቀጣይ አቅጣጫዎች የሚቀመጡበት መሆኑ ተገልጿል።

የመድረኩን መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የካፋ ዞን ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጋዎ አባመጫ፤ “Climate Resilient Forest Livelihood Program” (CRFL) ፕሮጀክት በሀሳብና በሀብት የደን ጥበቃ ተግባራትን ሲደግፍ ቆይቷል ሲሉ ገልጸዋል።

በደን ጥበቃ የተደራጁ ማህበራትንና ሌሎችንም በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ላይ የሚሰሩ አካላትን ተግባራት ለማስቀጠል መድረኩ ፋይዳ አለው ብለዋል።

የካፋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ደመላሽ ንጉሤ በበኩላቸው፤ ደን በካፋ ማህበረሰብ ልዩ ቦታ የሚሰጠውና ተጠብቆ እንዲቆይ በሚያደርጉ ባህሎች የቀጠለ መሆኑን ተናግረዋል።

ደንን መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ከጥበቃ ስራዎች ተጠቃሚ ለመሆን መስራት ግድ የሆነበት ጊዜ ላይ ተደርሷል ነው ያሉት።

የአየር ንብረት ለውጥ የዓለም ትልቁ አጀንዳ መሆኑን ተናግረው፤ የደን ጥበቃ ስራ ዘላቂ ተጠቃሚነትን የሚያስገኝ በመሆኑ የሁሉንም ትብብር ይጠይቃል ብለዋል።

CRFL በደን ጥበቃ ዙሪያ የሰራቸው ስራዎች ተጨባጭ ውጤት ማምጣታቸውን ገልጸዋል።

በክልሉ ደን፣ አካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኢንጂነር አስራት ገብረማሪያም እንደተናገሩት፤ መድረኩ ጉድለቶች ታርመው ቀጣይ ስራዎችን ለማሣካት የሚያስችል መግባባት የሚፈጠርበት ነው።

አካባቢው ዓለም-አቀፍ ተመራማሪዎችን እና ባለሀብቶችን ለመሣብ የሚያስችል የተፈጥሮ ጸጋ የሚገኝበት መሆኑን አንስተዋል።

CRFL እነኚህ ሀብቶች ተጠብቀው እንዲቀጥሉ በመስራት፣ የእውቀት ሽግግር በማድረግና ግልፅ የአሰራር ስልትን በመከተል ውጤታማ ፕሮጀክት እንደሆነ አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ ፍላጎትና በለጋሾች ይሁንታና ስምምነት CRFL እና REDD+ የተሰኙ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ተዋህደው እንዲሰሩ መደረጉን ገልጸዋል።

ከዞን አልፎ በክልል ደረጃ ውጤታማ ለመሆንና የተጀመሩ ስራዎችን ለማስቀጠል እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

“Climate Resilient Forest Livelihood Program” (CRFL) ከዚህ በኋላ በሚኖሩ ስራዎች በREDD+ ስር ሆኖ እና በከልላዊ ተቋምነት እንደሚቀጥል ታውቋል።

በመድረኩ የካፋ ዞን የተለያዩ መምሪያዎችና የክልል ቢሮዎች ኃላፊዎችና ምክትል ኃላፊዎች፣ በካፋ ዞን የ9 ወረዳዎች አስተዳዳሪዎችና የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃን ኃላፊዎች እየተሳተፉ ነው።

ዘጋቢ፡ ዮሐንስ ክፍሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን