በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለመጀመሪያ ጊዜ በተሰጠዉ ክልላዊ የ6ኛ ክፍል ፈተና ከተፈተኑ ተማሪዎች 75 በመቶ የሚሆኑት አልፈዋል- አቶ አንተነህ ፈቃዱ

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለመጀመሪያ ጊዜ በተሰጠዉ ክልላዊ የ6ኛ ክፍል ፈተና ከተፈተኑ ተማሪዎች 75 በመቶ የሚሆኑት አልፈዋል- አቶ አንተነህ ፈቃዱ

ሀዋሳ፣ ሐምሌ 23/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለመጀመሪያ ጊዜ በተሰጠዉ ክልላዊ የ6ኛ ክፍል ፈተና ከተፈተኑ ተማሪዎች 75 በመቶ የሚሆኑት ማለፋቸዉን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምሀርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ ገለፁ።

በክልሉ ከ30 ዓመት በኋላ በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ለመጀመሪያ ጊዜ በተሰጠዉ የ6ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ከተፈተኑ 85 ሺህ 547 ተማሪዎች  75 በመቶ ማለፋቸዉን የገለፁት ኃላፊዉ የማለፊያ ነጥብ 50 ከመቶና በላይ እንዲሁም ለአካል ጉዳተኞች 45 ከመቶና በላይ መሆኑን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል፡፡

ከተፈተኑ ተማሪዎች ወንድ 75.8 በመቶ ሴት 74.1 በመቶ ማለፋቸዉን ገልፀዋል፡፡

ክልል አቀፍ የ6ኛ ክፍል ፈተና ካስፈተኑ 1803 ትምህርት ቤቶች 424 (23.5 በመቶ) ሙሉ በሙሉ ተማሪዎችን አሳልፈዋል ያሉት አቶ አንተነህ ፈቃዱ 1490 ወይም 82.6 በመቶ ትምህርት ቤቶች ደግሞ ከግማሽ በላይ ተማሪዎችን አሳልፈዋል ብለዋል፡፡

19 ትምህርት ቤቶች ወይም 1 በመቶ የሚሆኑት ምንም ተማሪ ያላሳለፉ በመሆናቸዉ በቀጣይ በነዚህ ትምህርት ቤቶች ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡

በተሰራዉ ስራ የተኘዉ ዉጤት የተሻለ መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊዉ  ከቁልፍ ባለድርሻ አካላት ጋር በመግባባት ወደ ተግባር መገባቱ ለዉጤቱ መገኘት አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የትምሀርት ቤት አመራር ሪፎርም መደረግ፣ ትምህርትን በጊዜ ጀምሮ ማጠናቀቅ፣ ጠንካራ ድጋፍና ክትትል ስራዎች፣ ለተማሪዎች ክልል አቀፍ ሞዴል ፈተና ተዘጋጅቶ መሰጠቱና ሌሎችም ተግባራት ለተገኘዉ ዉጤት አስተዋጽኦ ማድረጉንም ጠቅሰዋል፡፡

ከተማሪዎች ጀምሮ ለተገኘዉ ዉጤት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላትም የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የማህበራዊ ክላስተርና የክልሉ ትምሀርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ:- ድልነሳዉ ተደሰ