ነገ ሐምሌ 24/2017 ዓ.ም በሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ የአንድ ጀንበር ተከላ ላይ ህብረተሰቡ በንቃት እንዲሳተፈ ጥሪ አቀርባለሁ – ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ
ሀዋሳ፡ ሐምሌ 23/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ነገ ሐምሌ 24/2017 ዓ.ም በሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ የአንድ ጀንበር ተከላ ላይ ህብረተሰቡ በንቃት እንዲሳተፈ ጥሪ አቀረቡ፡፡
ሙሉ መልዕክታቸው እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
“በመትከል ማንሰራራት”
በነገው የሐምሌ 24/2017 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ የአንድ ጀንበር ተከላ ሌላ ታሪክ እናስመዘግባለን፡፡
ባለፈዉ ዓመት በ6ኛው የሀገራዊው የአንድ ጀንበር ተከላ በክልላችን 55 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል አቅደን ተፈጥሮን ለመንከባከብ በማይሰንፈው ህዝባችን የነቃ ተሳትፎ ከዕቅድ በላይ 64 ሚሊዮን ችግኝ በመትከል አዲስ ታሪክ ማስመዝገብ መቻላችን የሚታወስ ነዉ።
በነገው ዕለት በሚካሄደው በሀገር አቀፍ ደረጃ በአንድ ጀንበር 700 ሚሊዮን ችግኞች ተከላ አካል የሆነው የክልላችን 60 ሚሊዮን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን በመትከል የድርሻችንን በማበርከት ሌላ ታሪክ ልናስመዘግብ ይገባል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተጎዱ ሥነ-ምህዳሮችን መልሶ በማልማት የአፈር ለምነትንና የገፀ ምድርና የከርሰ ምድር የውሀ ሃብታችንን በማጎልበት ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ፤ የተፈጥሮ አደጋ ተጋላጭነትንና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን በመግራት ለአረንጓዴ ምጣኔ ሀብት ግንባታ ግባችን ስኬት ሚናው እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡
ለዚህም በክልላችን ባለፉት ጊዜያት ባከናወናቸው የአረንጓዴ አሻራና የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራዎች ያስመዘገብነው አመርቂ ውጤት ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጂነት ለመላቀቅ ለምናደርገው ጥረት ውጤታማነት በማበርከት ላይ ያለው የጎላ አስትዋጽኦ በቂ ማሳያ ነው፡፡
ከዚህም በላይ ለናዳና መሰል የተፈጥሮ አደጋዎች ተጋላጭ የሆነ ሥነ-ምህዳር በሚበዛው ክልላችን በአረንጓዴ አሻራ በንቃት በመሳተፍ አሻራችንን ማኖር የህልውና ጉዳይ አድርገን እንድንነሳ የሚያስገድደን በመሆኑ፤ መላው የክልላችን ህዝብ እንደተለመደው በዘንድሮ የአንድ ጀንበር ተከላም በንቃት በመሳተፍ አረንጓዴ ከባቢን ለትውልድ ለማሻገር የጀመርነውን ጥረት እንድናጠናክር አደራ ለማለት እወዳለሁ፡፡
ለዚህም በዕለቱ በየአካባቢው በተዘጋጁ የተከላ ቦታዎች ማልዳችሁ በመገኘት በአንድ ጀንበር የተከላ መርሃ ግብራችን ከማለዳው 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት በከፍተኛ የባለቤትነት ስሜት በንቃት በመሳተፍ ታሪክ እንድትሰሩ ስል ከአደራ ጭምር ጥሪ አስተላልፋለሁ፡፡
በኅብረት የአካባቢያችንን ደህንነት በአረንጓዴ አሻራችን እናረጋግጣለን!
ምንጭ፡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት

More Stories
የቡርጂ ዞን ምክር ቤት አቶ ትንሳኤ ዮሐንስ ወጌ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አድርጎ ሾመ
የወባ በሽታ ስርጭትን የመከላከልና የመቆጣጠርን ጉዳይ ቀዳሚ ተግባር አድርጎ እየሰራ መሆኑን የስልጤ ዞን ጤና መምሪያ አስታወቀ
አገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን ተገልጋዩን ለማርካት እየሰራ መሆኑን የአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል አስታወቀ