በየደረጃው የሚገኙ ምክር ቤቶች ለውጥና ዕድገት ሊያመጡ በሚችሉ ጉዳዮች ዙሪያ በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባ የዳዉሮ ዞን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አሳሰቡ

በየደረጃው የሚገኙ ምክር ቤቶች ለውጥና ዕድገት ሊያመጡ በሚችሉ ጉዳዮች ዙሪያ በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባ የዳዉሮ ዞን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አሳሰቡ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 22/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በየደረጃው የሚገኙ ምክር ቤቶች ለኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ለውጥና ዕድገት ሊያመጡ የሚችሉ ጉዳዮች ላይ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ የዳዉሮ ዞን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አሳሰቡ፡፡

የዳዉሮ ዞን ምክርቤት 4ኛ ዙር 12ኛ የሥራ ዘመን፣ 27ኛ መደበኛ ጉባዔ እየተካሄደ ነው።

በጉባዔው ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የዳዉሮ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ዳዊት ሚኖታ፥ ምክር ቤቶች የሕዝብ ሉዓላዊነት መገለጫዎችና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት በመሆናቸው ለአገራዊ ለውጥና ዕድገት ወሳኝ የሆኑ አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎችን እንዲሁም በመንግሥት የሚታወጁ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች መተግበራቸው ቁጥጥርና ክትትል ያደርጋሉ ብለዋል።

ከዚህ የተነሣ የዞኑ ምክር ቤት በአስፈፃሚ አካላት የሚከናወኑ ለሕዝቡ ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጡ ተግባራትን በመገምገም አቅጣጫ በማስቀመጥ ውሳኔን የማስተላለፍ ሥራ እየሠራም እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የዞኑ ምክር ቤት ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ፀሐይ አየለ በበኩላቸው፥ በዞኑ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የተከናወኑ ተግባራትን ለምክር ቤት አባላት ያቀረቡ ሲሆን፥ በቋሚ ኮሚቴዎች በኩል የአስፈጻሚ አካላትን ተግባር በመገምገም እና የልማት ሥራዎችን የመስክ ምልከታ ያደረጉ ሲሆን ማስተካከያ የሚደረግባቸውን ውሳኔ ማስተላለፍ መቻሉንም አስረድተዋል።

ለሁለት ተከታታይ ቀናት በሚካሄደው የዳውሮ ዞን ምክር ቤት 4ተኛ ዙር 12ተኛ ሥራ ዘመን 27ኛ መደበኛ ጉባኤ የአስፈፃሚ አካላት የ2017 በጀት ዓመት ማጠቃለያ ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት እና የ2018 በጀት ዓመት ጠቋሚ ዕቅድ መርምሮ ማፅደቅ፣ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የ2017 በጀት ዓመት ማጠቃለያ አፈፃፀም ሪፖርት እና የበጀት ጥያቄ ቀርቦ መርምሮ ማፅደቅ፣ የዞኑ መንግስት የ2018 በጀት ዓመት የበጀት ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ማፅደቅ፣ የዳውሮ ዞን ምክር ቤት አባላት አዲስ የአባላት አሰራርና ሥነ ምግባር ደንብ መርምሮ ማጽደቅ እና የተለያዩ ሹመቶችን መስጠትና ማጽደቅ ናቸው ተብሎ ይጠበቃል።

ዘጋቢ፡ እታገኝ ዘነበ – ከዋካ ጣቢያችን