በአንድ ጀምበር ከ470 ሺህ በላይ ችግኞች ይተከላሉ – ጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት

በአንድ ጀምበር ከ470 ሺህ በላይ ችግኞች ይተከላሉ – ጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 22/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም በአንድ ጀምበር ከ 470 ሺህ በላይ ችግኞች ለመትከል የሚያስችሉ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት አስታወቀ።

‎በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም በአንድ ጀምበር ከ470 ሺህ በላይ የተለያዩ ለምግብነትና ሁሉ አቀፍ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን ለመትከል ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ገልጿል።

‎የይርጋጨፌ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ክፍሌ ጅክሶ ላለፉት ስድስት ዓመታት በመላው ሀገሪቱ ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም በርካታ ለውጦችን እያስመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።

‎የአረንጓዴ አሻራ የደን ሽፋን ለማስፋትም ሆነ ለማስጠበቅ ፣ ዝናብን በወቅቱ ለማግኘት፣ ለተስተካከለ ስነምህዳር እና ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ያለው አስተዋጽዖ ከፍተኛ እንደሆነም ገልጸዋል ።

‎በይርጋጨፌ ወረዳ የሀገር በቀል ዛፎችንና ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችን በብዛት መትከል ላይ ትኩረት መደረጉንና ከነዚህም መካከል የደረሱ ፍራፍሬዎች እንዳሉ ነው የጠቆሙት ።

‎ዘንድሮም በአንድ ጀምበር ከ470 ሺህ በላይ የተለያዩ ዝሪያ ያላቸውን ችግኞችን በ490 ነጥብ 5 ካሬ መሬት ላይ ለመትከል መዘጋጀታቸውን ጠቁመው፥ ለዚህም የሚሆኑ ሀገር በቀል ዛፎችን ጨምሮ የፍራፍሬ፣ የቡና፣ የእንሰትና ሌሎችም ችግኞች በበቂ ሁኔታ መዘጋጀታቸውንና በ18ቱም ቀበሌዎች ላይ ለመትከል አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።

‎ለሀገር አሻራችንን የምናሳርፍበት ቀን በመሆኑ ህብረተሰቡ በነቂስ ወጥቶ በችግኝ ተከላ ፕሮግራም ላይ መሳተፍ አለበት ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል ።

‎ዘጋቢ፡ ለምለም ኦርሳ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን