የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተከናወኑ ተግባራትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ መሰረተ ልማትና የመንግስት ሀብት ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስገነዘበ

የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተከናወኑ ተግባራትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ መሰረተ ልማትና የመንግስት ሀብት ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስገነዘበ

ቋሚ ኮሚቴው የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምን ገምግሟል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለክልሉ ምክር ቤቱ የፕላን፣ መሰረተ ልማትና የመንግስት ሀብት ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርቦ ተገምግሟል።

ቢሮው በበጀት ዓመቱ ያከናወናቸው ሰው ተኮር ተግባራት አበረታች እንደሆኑ የገለፁት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ታመነ ገብሬ፤ የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተጀመረው የሰንበት ገበያ ስራን በማጠናከር አቅራቢውንና ሸማቹ ማህበረሰብን ከማቀራረብ በተጨማሪ ለጥራቱ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል ብለዋል።

የምርት እጥረት እንዳይኖር የተሻለ አሰራርን ዘርግቶ መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል።

በነዳጅ ምርት አቅርቦትና ስርጭት ላይ የሚታዩ ጉድለቶችን በቀጣይ ለማረም ቅንጅታዊ ስራዎችን በማጠናከር ህገ ወጥ አሰራርን ለመከላከል እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም አቶ ታመነ ጠቁመዋል።

የፍጆታ ምርቶችን ለህብረተሰቡ ከማቅረብ አኳያ የተሰሩ ስራዎች አበረታች ቢሆኑም በቀጣይ እጥረት እንዳይኖር ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት ሰብሳቢው፡፡

የተጀመሩ የግብይት ማዕከላት ግንባታ አገልግሎት እንዲሰጡ ተቀናጅቶ መስራት እንደሚጠይቅም ጠቁመዋል። እነዚህንና ሌሎችም ከምክር ቤቱ የፕላን፣ መሰረተ ልማትና የመንግስት ሀብት ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠው ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ዘጋቢ፡ ሪድዋን ሰፋ – ከወልቂጤ ጣቢያችን