ተመራቂ ተማሪዎች የመንግስትን ስራ ከመጠበቅ ወጥተው ስራ ፈጥረዉ በመስራት ለሀገር ዕድገት የድርሻቸውን መወጣት እንደሚገባቸው ተገለፀ

ተመራቂ ተማሪዎች የመንግስትን ስራ ከመጠበቅ ወጥተው ስራ ፈጥረዉ በመስራት ለሀገር ዕድገት የድርሻቸውን መወጣት እንደሚገባቸው ተገለፀ

አትላስ የቢዝነስ እና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ሆሳዕና ካምፓስ በቴክኒክና ሙያ ዘርፎችና በመጀመሪያ ዲግሪ ለ15ኛ ዙር በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸውን 490 ተማሪዎችን አስመርቋል።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የአትላስ ቢዝነስና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ የሆሣዕና ካምፓስ ዲን አቶ ታደሰ ማቴዎስ እንዳሉት፤ ኮሌጁ በመማር ማስተማር፣ በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎቶች በርካታ ስራዎችን እየሰራ ነው።

ለሁሉም የኮሌጁ ተመራቂ ተማሪዎች ለወላጆችና ለኮሌጁ መምህራን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክትም አስተላልፈዋል።

የአትላስ ቢዝነስ እና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ፕሬዝዳንትና ባለቤት ዶክተር ታጋይ ሚፍታ በበኩላቸው፤ ኮሌጁ በአገሪቱ በተለያዩ ክልሎች በሚገኙ 10 ካምፓሶች ብቁና ተወዳዳሪ ዜጎችን በማፍራት ለሀገር እያበረከተ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኮሌጁ የመንግስትን የትምህርት ፖሊሲ መሰረት በማድረግ ለትምህርት ጥራት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ዶክተር ታጋይ ገልጸዋል።

ከ490 ተመራቂ ተማሪዎች ውስጥ 310 ሴቶች ሲሆኑ 25 ተማሪዎች በኮሌጁ ነፃ የትምህርት ዕድል ያገኙ መሆናቸዉንም ዶ/ር ታጋይ ገልጸዋል።

የዕለቱ ተመራቂዎችም በኮሌጅ ቆይታ የቀሰሙትን እውቀት በመጠቀም ራሳችሁን ከሙስናና ከብልሹ አሰራር ነፃ በማድረግ ሀገራቸውን በታማኝነትና በቅንነት ማገልገል እንደአለባው ዶ/ር ታጋይ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የእለቱ የክብር እንግዳ የሀዲያ ዞን የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና መምሪያ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ እርስቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ መንግስት በሰጠው ልዩ ትኩረት የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በትምህርቱ ዘርፍ በርካታ ምሁራንን እያፈሩ እንደሚገኙ በመግለጽ አትላስ የቢዝነስና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ የሆሣዕና ካምፓስ ስራ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንዳሚገኝ ተናግረዋል።

የእለቱ ተመራቂዎችም የመንግስትን ስራ ጠባቂዎች ሳይሆኑ ስራ ፈጣሪዎች በመሆን ከተቀጣሪነት አስተሳሰብ መዉጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ኮሌጁ በዕለቱ ለ16 አቅመ ደካማ ቤተሰብ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል::

በተማሪዎች ምረቃ ፕሮግራም ላይ የተገኙት የሀዲያ ዞን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ እቴነሽ ሙሉጌታ እና የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ በረከት ታደሰ እንዳሉት፤ ኮሌጁ በማህበረሰብ አገልግሎት ሰዉ ተኮር ተግባራትን እያከናወነ መሆኑ የሚበረታታ ነዉ።

አንዳንድ የእለቱ ተመራቂዎች በበኩላቸው በሰለጠኑበት የሙያ ዘርፍ ህዝብንና ሀገርን በቅንነት ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በዕለቱ በትምህርታቸው ከፍተኛ ዉጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ዘጋቢ: ተሻለ ከበደ – ከሆሳዕና ጣቢያችን