“በክልሉ ከ58 ሺህ 364 በላይ ኩነቶች ተመዝግበዋል” – አቶ አበበ ከበደ

በመለሠች ዘለቀ

ንጋት፡- ለቃለ መጠይቃችን ፈቃደኛ ስለሆኑ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ፡፡

አቶ አበበ፡- እኔም ስለተሰጠኝ እድል አመሰግናለሁ፡፡

ንጋት፡- ስለ ወሳኝ ኩነቶች ምንነት በማንሳት እንጀምር?

አቶ አበበ፡- ወሳኝ ኩነት ማለት የሰው ልጅ ከተወለደበት እስከ ሚሞትበት ጊዜ ባለው የህይወት ሂደት ውስጥ የሚከሰቱ ሁነቶች ናቸው፡፡ እነዚህም ልደት፣ ጋብቻ፣ ፍቺ፣ ጉድፈቻና ሞት በመባል ይታወቃሉ፡፡ ልደትና ሞት፣ ጋብቻና ፍቺ የሰው ልጅ ሕይወት የሚጀመርባቸውና የሚጠናቀቅባቸው እንዲሁም የሚያልፍባቸው የሕይወት ኩነቶች ናቸው፡፡

እነዚህ ክስተቶች ወሣኝ ኩነቶች የተባሉበት ዋናው ምክንያት በየአገሮች ሕገ-መንግሥትና በዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች የታወቁ የሰብዓዊ፣ የማኅበራዊና የፖለቲካ መብቶችን ተፈጻሚ ለማድረግና ለመጠበቅ ወሳኝ የሆኑ ሕጋዊ የግለሰብ ማንነት መረጃዎች ምንጭ በመሆናቸው ነው፡፡

ከዚህ ባሻገር ኩነቶቹ የአንድን አገር ሕዝብ ብዛትና ዕድገትን በትክክል ስለሚያሳዩ፣ ለኅብረተሰቡ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ባሕላዊ አገልግሎት አሰጣጥ ለሚዘጋጁ ዕቅዶች ዝግጅትና አፈጻጸም ተፈላጊና ወሳኝ መረጃዎች በመሆናቸው ወሳኝ ኩነት ተብለዋል፡፡ ኩነቶቹ በአንድ አገር ዜጎች የሰብዓዊ መብትና የፍትሕ አስተዳደር እንዲሁም የማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ አገልግሎት አሰጣጥ ካላቸው ቁልፍ ሚና በመነሳት ኩነቶቹ ሲከሰቱ ማለትም አንድ ሰው ሲወለድ፣ ሲያገባ፣ ሲፋታ ወይም ሲሞት የሚመዘገብበት፣ የሚደራጅበት እና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውልበት የአመዘጋገብና የመረጃ አጠነቃቀር ሥርዓት የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ በመባል ይታወቃል፡፡ “ልደትና ሞት በሰው ልጅ ላይ አንድ ጊዜ የሚከሰቱ ተፈጥሮአዊ ክስተቶች ናቸው። ሰዎች በልደት አማካይነት ወደ ዓለም ኅብረተሰብ ይቀላቀላሉ፤ በአንጻሩ በሞት አማካይነት ከዓለም ይለያሉ፡፡ በመሆኑም ልደትና ሞት በሰው ልጅ አፈጣጠርና አኗኗር የሕይወት መነሻና መድረሻ እርከኖች መለያ ናቸው፡፡

ስለሆነም ልደት በዚህች ምድር የሰዎች የመኖር ሕጋዊ መብት ምንጭ ኩነት በመሆኑ ማንኛውም ሰው በአንድ በታወቀ ሕጋዊ የዜግነት ማንነት መብት የሚያገኝበትና ለዚህም ማረጋገጫ የሚሆነውን ሕጋዊ ሰነድ በመንግስት የሚዘጋጅበት የህይወቱ የመብት መነሻ እርከን ሲሆን በአንጻሩ ሞት የዚህ መብት መጨረሻ እርከን ነው፡፡

ንጋት፡ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አስፈላጊነት እንዴት ይለጻል?

አቶ አበበ፡- በአገሪቱ ፍትሕ አስተዳደር የግለሰብና የቤተሰብ ጉዳይ የፍትሕ አገልግሎት አሰጣጥ ወሳኝ ክስተቶች መሆናቸው፣ ከሥነ-ህዝብ ለውጥ ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት ያላቸውን የሕዝብ ብዛትና እድገት ስለሚያሳዩ፣ በእነዚህም ላይ ተመሥርቶ ለኅብረተሰቡ ጥቅም ለሚከናወኑ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ እቅዶችና አስተዳደራዊ አገልግሎቶች ዝግጅት የመረጃ መሠረት በመሆናቸው ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው፡፡

በአዋጁ ሰው ከተወለደበት ቀን አንስቶ እስከ ሚሞትበት ቀን ድረስ የሕግ መብት አለው በማለት ተደንግጓል፡፡ በሌላም በኩል ጋብቻና ፍቺ ሰው “ህጋዊ ሰው” የመሆን መብት በሚያገኝበትና በሚያጣበት የማኅበረሰባዊ አኗኗር ሥርዓት ውስጥ የሚከሰቱ ዋነኛ የሰዎች ማኅበረሰባዊና ሕጋዊ አቋም ለውጥ ጠቋሚ ወሳኝ ኩነቶች ናቸው፡፡

እነዚህ በግለሰቦች ላይ የሚከሰቱ ተፈጥሮአዊና ማኅበረሰባዊ ለውጦች የአንድን አገር አልፎም የአስተዳደር ክፍል የህዝብ አስተዳደር በሥርዐት ለመምራት መነሻ መሰረቶች ናቸው፡፡ ልደትና ሞት የህዝብ ብዛትና እድገትን በቀጥታ ከሚያሳዩ ክስተቶች ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ይኼውም የህዝቡ ቁጥር መጨመር፣ መቀነስ ወይም ባለበት መቆየቱ የሚታወቀው በአንድ ሀገር በሚከሰተው የልደትና ሞት ኩነት ብዛት ነው፡፡

በተመሣሣይ ጋብቻና ፍቺም የአንድ ሀገር ህዝብ ብዛትና እድገት መጨመርን ወይም መቀነስን በተዘዋዋሪ ከሚወስኑ ሁኔታዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ጋብቻ የአንድ ኅብረተሰብ መሠረት እንደመሆኑ መጠን ምንም እንኳን ከጋብቻ ውጪ የሚከሰት የልደት ኩነት ቢኖርም በአብዛኛው የልደት ኩነት የሚከሰተው ኅብረተሰቡ ከሚመሠርታቸው ጋብቻዎች ነው፡፡ በአንፃሩ የፍቺ ኩነቶች በተከሰቱ ቁጥር የልደት ኩነቶችም በዚያው መጠን ይቀንሳሉ። በተመሣሣይ መልኩ የልደትና የሞት ኩነቶች ክስተት በቀነሰ ቁጥር የህዝብ ቁጥር እድገትም በዚያው መጠን ይቀንሳል፡፡

ንጋት፡- የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አጀማመር እንዴት ይገለጻል?

አቶ አበበ፡- አዋጅ ቁጥር 760/2004 የወሳኝ ኩነት ምዝገባና የብሔራዊ መታወቂያ አዋጅ በ2004 ዓ.ም ወጥቷል፡፡ ይህም ከ2008 ዓ.ም ሀምሌ ወር ጀምሮ በሁሉም አካባቢዎች ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡

ይህ አዋጅ በመላ ሀገሪቱ ባሉ አካባቢዎች ወይም በማንኛውም ኢትዮጵያዊ ላይ ተፈፃሚ የሚሆን ሲሆን በአዋጁ የወሳኝ ኩነት መረጃዎች የሚመዘገቡት መዝገብ የክብር መዝገብ ተብሎ የተተረጎመ ሲሆን አዘገጃጀቱ በቋሚነት ለማገልገል በሚችል፣ ለአያያዝ በሚያመች በጥራዝ መልክ ሆኖ ለእያንዳንዱ የወሳኝ ኩነት ዓይነት የተለየ የክብር መዝገብ እንደሚኖረው ተደንግጓል፡፡

በአዋጁ ማንኛውም ወሣኝ ኩነት መመዝገብ እንዳለበትና ኩነቱም አንድ ጊዜ ብቻ መመዝገብ እንዳለበት በግልጽ ተመላክቷል፤ ይህ ማለት ከተጋቡ፣ ወይም ከተፋቱ ወይም ልጅ ከወለዱ ኩነቱን የማስመዝገብ ኃላፊነት አለብዎት ማለት ነው። ወሣኝ ኩነት ሲከሰት እንዲያስመዘግብ ኃላፊነት ወይም ግዴታ የተጣለበት አስመዝጋቢ በአቅራቢያ በሚገኝ የምዝገባ ጽ/ቤት በመገኘት ኩነቱን የማስመዝገብ ግዴታን አለመወጣት ለልዩ ልዩ ኃላፊነቶች ያጋልጠዎታል ማለት ነው፡፡

በአዋጁ በግልጽ እንደተቀመጠው አምስቱንም ኩነቶች በሶስት ከፍሎ ነው ሂደቱ የሚከናወነው፡፡ አንደኛው ሁነቱ በተከሰተበት ወቅት የሚመዘገብ ሲሆን ሌላኛው በተለያዩ የጊዜ ገደቦች ማለትም ልደት ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ 90 ቀናት ድረስ ጋብቻ፣ ፍቺ፣ ሞት እና ጉዲፈቻ በአንድ ወር ገደብ ውስጥ መመዝገብ አለባቸው፡፡ እስከ አንድ አመት እና ከዚያ በላይ የቆየ ምዝገባ የዘገየ ተብሎ ይያዛል፡፡ ምዝገባው የሚካሄደው በቀበሌ ደረጃ ሲሆን ኩነቱን ሊያስመዘግብ የሚመጣው አካል ማንነቱን የሚገልጽ መታወቂያ መያዝ ይኖርበታል፡፡

ቀደም ሲል ልደቱን ማስመዝገብ የሚችሉት ወላጅ እናቱና አባቱ በቦታው ተገኝተው የነበረ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ግን በመመሪያው መሰረት ከሁለት አንዳቸው ተገኝተው ማስመዝገብ ይችላሉ፡፡ የወሣኝ ኩነቶች ምዝገባ ሁሉን አቀፍ፣ ቀጣይ፣ ቋሚና አስገዳጅ የምዝገባው ልዩ ባህሪይ በመሆኑ ህብረተሰቡና የማስመዝገብ ኃላፊነት የተጣለባቸው ሌሎች አካላት ምዝገባውን እንዲያከናውኑ የጊዜ ገደብ ተመልክቷል፡፡

በዚህም መሠረት የኢትዮጵያን ማህበራዊ፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ሁኔታዎች ከግምት በማስገባት ሊያዘገይ የሚችል በቂ ምክንያት ከሌለ በስተቀር ማንኛውም ወሣኝ ኩነት ከልደት በስተቀር ከተከሰተበት ወይም ከተፈፀመበት ቀን ጀምሮ በ30 ቀናት ውስጥ መመዝገብ እንዳለበት በአዋጁ ተመልክቷል፡፡

ንጋት፡- የምዝገባው ሂደቱን በቴክኖሎጂ የማስደገፍ ስራ ምን ይመስላል?

አቶ አበበ፡- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰባት ዞኖችና ሶስት ልዩ ወረዳዎች የሚገኙ ሲሆን በክልሉ በ1 ሺህ 314 ቀበሌያትና በ25 ሆስፒታሎች ላይ የልደት ምዝገባ እንዲካሄድ ተደርጓል፡፡ እያንዳንዱ ቀበሌ ከፌደራል መረጃ ቋት ጋር የተሳሰረ ኮድ አላቸው፡፡ የክልሉ መዋቅር አዲስ እንደመሆኑ መጠን በ2017 ዓ.ም ብቻ ለ700 መዝገብ ሹሞች ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

ንጋት፡- ስለ ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አስፈላጊነት ዙሪያ የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ ስራ ምን ይመስላል?

አቶ አበበ፡- ከ2015 ዓ.ም ከክልሉ አደረጃጀት በመቀጠል ተቋሙ በ2016 ዓ.ም ወደ ስራ ሲገባ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም የግንዛቤ ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ለአብነትም ያለንን ውስን ሀብት በመጠቀም በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች ላይ ግንዛቤ የማሳደግ ስራ እየተሰራ ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ የምዝገባ ሽፋን እያደገ መጥቷል፡፡

በክልሉ ከ7 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የሚኖር ሲሆን ከዚህም ቢያንስ ከ30 እስከ 40 ከመቶ የልደት የምስክር ወረቀት ይፈልጋል። የክልሉ ማህበረሰብ ወደ ውጭ የመውጣት እድሉ ሰፊ ነው፡፡ ለዚህም ፓስፖርት ለማውጣት የልደት የምስክር ወረቀት መያዝ ግዴታ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የልደት ምዝገባ ሽፋን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል፡፡

ንጋት፡- የሁነቶቹን ምዝገባ ውጤታማ ለማድረግ የባላድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር እንዴት ይገለጻል?

አቶ አበበ፡- የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በርካታ ናቸው፡፡ ከእነዚህም አንዱና ዋናው ባለድርሻ የጤና ተቋም ነው፡፡ የጤና ተቋማት ህጻናት ሲወለዱ የእቅዳቸው አካል አድርገው እንዲመዘግቡ በቅንጅት እንሰራለን፡፡ ፍርድ ቤቶችም ከፍቺና ከጉዲፈቻ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን እንዲያስፈጽሙ በጋራ እንሰራለን፡፡ ተማሪዎች ቅድመ መደበኛ ትምህርት ለመመዝገብ የልደት የምስክር ወረቀት መያዝ ስላለባቸው ይህንን ለማጠናከር ከመንግስትና ከግል የትምህርት ተቋማት ጋር በቅንጅት እንሰራለን፡፡

በክልሉ ሰባት የሀይማኖት ተቋማት የሚገኙ ሲሆን ስለ ምዝገባው ግንዛቤ ለማሳደግ ከእነዚህ ተቋማት ጋር በጋራ እየሰራን እንገኛለን፡፡ የልደት ምዝገባ ከህጻናት መብቶች አንዱ በመሆኑ ይህንን ለማረጋገጥ ከሴቶችና ህጻናት ተቋማት ጋር በህብረት እንሰራለን፡፡

ንጋት፡- በበጀት አመቱ እስካሁን ባለው እንቅስቃሴ የምዝገባው አፈጻጸም ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

አቶ አበበ፡- በበጀት አመቱ በ9 ወራት ብቻ ከእቅድ በላይ ማሳካት ችለናል፡፡ በ5 ዘርፎች 56 ሺህ 117 ኩነቶች ለመመዝገብ የታቀደ ሲሆን አፈጻጸሙም 58 ሺህ 364 ደርሷል፡፡ በቀጣይ ቀሪ ወራት የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል። የልደት ምዝገባ በጤና ተቋማት ላይ በነጻ ሲሆን በቀበሌ ደረጃ 20 ብር፣ የዘገየ 25 ብር፣ ሌላው 30 ብር ነው፡፡

ነገር ግን አንዳንድ የቀበሌ ስራ አስኪያጆች እስከ አንድ ሺህ ብር ድረስ እንደሚያስከፍሉ ጥቆማ ደርሶናል። እንደዚህ አይነት ህገ ወጥ ተግባራትን ለመከላከል ህብረተሰቡ ትብብር ማድረግ አለበት፡፡ ለዚህም የጥቆማ 6128 ነጻ የስልክ መስመር ተዘርግቷል፡፡

ንጋት፡- ስለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡

አቶ አበበ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡