በማረምያ ተቋም የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭትን በመከላከል የግንዛቤና ሌሎች ተግዳሮቶችን ለመፍታት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑ ተጠቆመ

በማረምያ ተቋም፣ በመንግስትና በግል የልማት ድርጅቶች ያሉ የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭትን በመከላከል የግንዛቤና ሌሎች ተግዳሮቶችን ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ከማረምያ ተቋም፣ ከመንግስትና ግል ድርጅቶች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከል እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በቅንጅት ለመስራት የሚያስችል ውይይት በጂንካ ከተማ አካሄደ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከል እና መቆጣጠር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ማቲዎስ ጋርሾ በንግግራቸው እንደገለፁት ለኤች አይ ቪ ኤድስ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ያሉትን የግንዛቤና ሌሎች ተግዳሮቶችን ለመፍታት ያለመ ነው ብለዋል።

አክለውም ለስርጭቱ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎችን በመለየት በኤች አይቪ እና ሌሎች በሽታዎች በተሰሩ ሥራዎች ሰፊ ለውጦች መምጣታቸውን የገለፁት ኃላፊው በቀጣይ የግብዓትና ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን በጋራ በመፍታት ለመስራት መግባባት የተፈጠረበትና በ2030 ኤች አይ ቪ የህብረተሰብ የጤና ስጋት ወደ ማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት በቅንጅት እየተሰራ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

የክልሉ ማረምያ ቤት ምክትል ኮሚሽነር ወንድማገኝ ሰለሞን በበኩላቸው በክልሉ ባሉ 8ቱም ማረምያ ተቋማት ውስጥ ሰፊ የታራሚ ቁጥር በመኖሩና በኤች አይ ቪ ኤድስ ተጋላጭ ከሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች አንዱ በመሆናቸው ተጋላጭነቱን ለመቀነስና መዘናጋቶችን ለመፍታት ትኩረት አድረጎ በመስጠቱ ቢሮውን አመስግነዋል።

የክልሉ ማረምያ ተቋም ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በኤች አይ ቪ ኤድስ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ተላላፊ በሆኑ በሽታዎች ዙሪያም በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ኮምሽነሩ አመላክተዋል።

በውይይቱ የመነሻ ሰነድ የቀረበ ሲሆን ከተሳታፊዎችም በተለይም በማረምያ ቤቶች በሂኘታይተስና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች የተያዙ ሰዎችን ለይቶ ማሰቀመጫ ቦታ አለመኖር፣ በኤች አይ ቪ ኤድስ የግንዛቤ ማነስ፣ የኮንዶም እጥረትና ሌሎችም ጉዳዮች ተነስተዋል።

የመድረኩ መሪዎችም የተነሱ ሃሳቦች ተገቢና ትክክለኛ በመሆናቸው ሁሉም የድርሻውን በመውስድ የጋራ በማድረግ በቅንጅት በመተጋገዝ እና በመናበብ ችግሮችን ለመቅረፍ እንዲሰራ አሳስበዋል።

አሰተያየታቸውን ከሰጡን መካከል የአርባምንጭ ማረምያ ተቋም አዛዥ ኮማንደር አለሙ ከንቶ ፣ የኣሪ ዞን ማረምያ ተቋም አዛዥ ምክትል ኮማንደር አስቻለው ነሬሬና ወ/ሮ መታሰቢያ አረጋው በጋራ በሰጡት አስተያየት የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት የግንዛቤ ሥራዎችን ከስልጠና ጀምሮ አርአያ እንዲሆኑ በማድረግ እየሠራ ሲሆን ይህ መድረክም በቀጣይ ከቢሮው ጋር በቅንጅት ለመስራት ያስችለናል ብለዋል።

ሌላኛው አሰተያየት ሰጪ ከኦሞ ኩራዝ ቀጥር ሁለት የኤች አይ ቪ አሰተባባሪ ደረጀ ወልደዮሐንስ መድረኩ በተለይም በመንግስት የልማት ድርጅቶች ያሉ መዘናጋቶችን ከምንይዘው የሰው ኃይል አንፃር ግብረኃይል ተቋቋሞ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችን እንድናጠናክር የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

ዘጋቢ: ከተማ በየነ ከጂንካ ጣቢያችን