በፋይናንስ ዘርፍ አሠራሮች ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማረም በ2018 ትኩረት እንደሚደረግ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፋይናንስ ቢሮ ገለጸ

በፋይናንስ ዘርፍ አሠራሮች ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማረም በ2018 ትኩረት እንደሚደረግ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፋይናንስ ቢሮ ገለጸ

ቢሮው የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2018 ዕቅድ ላይ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በቦንጋ ከተማ ምክክር አድርጓል።

የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ወሰነች ቶማስ የፋይናንስ ሴክተሩ የክልሉን ሀብት በአግባቡ በማስተዳደር የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይጠበቅበታል ብለዋል።

በተለይም በጥሬ ገንዘብ አስተዳደር ስርዓትን በመከታተል የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በ2018 በጀት ዓመት በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ የሚመደቡ በጀቶች ስራ ላይ ስለመዋላቸው ጥብቅ የክትትል ስርዓት ይዘረጋል ብለዋል።

የውስጥ ኦዲት ስርዓቱን ማጠናከር በዘርፉ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማረም ከፍተኛ ሚና እንዳለው የተናገሩት ወይዘሮ ወሰነች ፤ ተቋማት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በክልሉ በፋይናንስ ዘርፍ ለሚስተዋሉ ፍላጎቶች ምላሽ ለመስጠት የገቢ አቅምን ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን አንስተው ፤ የገቢ አቅም ክልሉ ሲመሰረት ከነበረበት 2.4 ቢሊዬን ወደ 10.4 ቢሊዬን ብር ማድረስ እንደተቻለ ጠቁመዋል።

በቀጣይም ሌሎች የገቢ አማራጮችን በተሟላ ሁኔታ በመሰብሰብ ለህብረተሰቡ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ይገባል ብለዋል።
የ2018 በጀት ዓመትን ዕቅድ ያቀረቡት በቢሮው የልማት ዕቅድ ባለሙያ አቶ ማስረሻ አየለ በበኩላቸው ፤ ዕቅዶችን በተናበበ መልኩ ተግባራዊ ማድረግ እንዲቻል የተቀናጀ ድጋፍና ክትትል ይደረጋል ብለዋል።

በፋይናንስ ሴክተሩ የሚከናወኑ አረንጓዴ አሻራ፣ የክልሉ ኢኒሼቲቮች፣ የክረምት በጎ አድራጎትና ለሌሎች የ90 ቀናት ዕቅዶችም ቀርበዋል።

በመድረኩ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላትም የመንግስት ፋይናንስን ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ በመምራትና ለሰብዓዊ አገልግሎቶች ቅድሚያ በመስጠት የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ዘጋቢ ፡ አሰግድ ሣህሌ-ከቦንጋ ጣቢያችን