ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ የንግድ ትርፍ ግብርን አሳውቃ ያልከፈለችው ግለሰብ በእስራትና በገንዘብ ተቀጣች
በኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ 25 ሚሊዮን 385 ሺ 666 ብር የንግድ ትርፍ ፍሬ ግብርን አሳውቃ ባልከፈለችው ግለሰብ ላይ ክስ አቅርቦባት በ2 ዓመት ጽኑ እስራት እና በ40 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ እንድትቀጣ አድርጓል፡፡
እመቤት መላኩ የተባለችው ተከሳሽ የታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 አንቀጽ 116/2/ እና 125/1/ን በመተላለፍ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አራዳ ክፍለ ከተማ በወረዳ 01 በግብር ከፋይ መለያ ቁጥር ተመዝግባ የንግድ ስራ ስትሰራ የቆየች ሲሆን በግብር ስወራ ወንጀል ከ2004 እስከ 2010 በተደረገው የኢንቨስትጌሽን ኦዲት ግብር ለመሰወር በማሰብ ግዥ ያልተፈጸመባቸው 72 ሀሰተኛ ደረሰኞችን ግዢ እንደተፈፀመባቸው በማስመሰል በሂሳብ መዝገብ ውስጥ በማካተት ለግብር ሰብሳቢው ተቋም በማሳወቅ የሚፈለግባትን አጠቃላይ የንግድ ትርፍ ግብር ፍሬ ግብር 25 ሚሊዮን 385 ሺ 666 ብር አሳውቃ ባለመክፈሏ በፈጸመችው የንግድ ትርፍ ግብር ስወራ ወንጀል ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቶባታል፡፡
ተከሳሿ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ ወንጀል ችሎት ቀርባ የተከሰሰችበት ክስ በችሎት ተነቦላት የወንጀል ድርጊቱን አልፈፀምኩም ጥፋተኛም አይደለሁም ያለች ሲሆን ዐቃቤ ህግም 2 የሰው ምስክሮችንና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ በበቂ ሁኔታ ያስረዳ በመሆኑ ተከሳሿ በቀረበባት ክስ መሰረት እንድትከላከል ብይን መሰጠቱን ከፍትሕ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በሰጠው ቀጠሮ መሰረት 1 የመከላከያ ምስክር አቅርባ ብታሰማም የአቃቤ ህግ ምስክሮችንና ማስረጃዎችን ማስተባበል ባለመቻሏ ትከላከል በተባለችበት ድንጋጌ ስር የጥፋተኛ ፍርድ በመስጠት በ2 ዓመት ጽኑ እስራትና በ40 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ እንድትቀጣ ሲል ወስኗል፡፡
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ