ለህብረተሰቡ የልማት ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ለመስጠት የገቢ አማራጮችን በማስፋት ገቢን አሟጦ መሰብሰብ እንደሚገባ ተገለጸ

በጎፋ ዞን የ2017 የግብር መክፈያ እና የ2018 በጀት ዓመት የንግድ ስራ ፈቃድ እድሳት ማስጀመሪያ የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል።

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ መድረኩን ሲከፍቱ እንዳሉት፤ የህብረተሰቡን የልማት ፍላጎት ለማሟላት የገቢ አማራጭችን በማስፋት ገቢን አሟጦ መሰብሰብ ይገባል።

ያሉትን ፀጋዎች የሚመጥን ገቢ መሰብሰብ ይገባል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፤ ይህን ለማሳካት የንግድ እና የገቢ ስርዓትን ማዘመን እንደሚገባም ተናግረዋል።

በታችኛው መዋቅር የሚገኙ የዘርፉ አመራርና ባለሙያዎች የንግድ እና የገቢዎች ስራ ማዘመን የሚያስችሉ የመሠረተ ልማት እና ቁሳቁስ የሟሟላት ስራ ቀዳሚ ተግባር አድርገው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የዞኑ ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ወልደሚካኤል መኮንን፤ መድረኩ ባለፈው አፈፃፀም ወቅት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በመለየትና መፍትሔ በማስቀመጥ በቀጣይ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የጎላ ፋይዳ አለው ብለዋል።

በተጠናቀቀው የግብር ዘመን በውስንነት የተስተዋለውን የገቢ ዘርፍ አፈፃፀም ለማሳደግ በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

በዞኑ በሚገኙ አንዳንድ ነጋዴዎች ዘንድ ደረሰኝ ከመስጠት አንፃር ውስንነት ይታያል ያሉት ኃላፊው፤ ችግሩን ለማረም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ በስፋት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የገቢና ስርዓቱን በማዘመን ዲጃታል ለማድረግ እየተሰራ ያለው ተግባር ዘርፈ ብዙ የአሰራር ጥሰቶችን ከማረም አንፃር የጎላ ፋይዳ ስላለው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አንስተዋል።

የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ትዝታ አብርሃም በበኩላቸው፤ በየደረጃው የሚገኙ የሴክተሩ አመራሮችና ባለሙያዎች ከንግድ ስራ ፈቃድ ዕድሳት ጋር ተያይዞ ከገቢ መዋቅሩ ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።

አገልግሎቶችን በኦንላይን በመስጠት በዘርፉ የሚስተዋሉ ሌብነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ አፅንኦት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በዞኑ የሚገኙ ከ9 ሺ 600 በላይ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች የ2017 ግብራቸውን ሲከፍሉ አያይዘው የንግድ ስራ ፈቃድ እንዲያድሱ ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት መድረኩ የተሻለ የገቢ አሰባሰብና የንግድ ስራ ፈቃድ ዕድሳት ተግባር ለማከናወን የጎላ ፋይዳ ስላለው ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ ለመሰብሰብ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን