ሀዋሳ፡ ሰኔ 20/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የመንግሥትን ግብር በታማኝነት በመክፈል ሁሉም ለሀገር ያለውን አጋርነት ማረጋገጥ እንደሚጠበቅበት የጌዴኦ ዞን ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ።
በጌዴኦ ዞን የ2017 ግብር ክፍያና የ2018 የንግድ ሥራዎች ፈቃድ ዕድሳት ማስጀመሪያ የንቅናቄ መድረክ በዲላ ከተማ ተካሂዷል።
የመምሪያው ኃላፊ አቶ ጌቱ ታምሩ ባቀረቡት ሪፖርት እንደገለጹት፣ ለአንድ ሀገር ዕድገትና ብልጽግና ግብር ብቸኛው አማራጭ መሆኑን በመጠቆም የዞኑን ልማትና ዕድገት ለማፋጠን ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች ግብርን በአግባቡ በመክፈል የበኩላቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
በ2017 የግብር ዘመን በ11 ወራት ከዲላ ከተማ አስተዳደር መዋቅር ውጪ 1 ቢሊዮን 484 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን በሪፖርቱ ተመልክቷል።
በተለይ በመብራት ዝርጋታ፣ በንጹሕ የመጠጥ ዉሃ አቅርቦት፣ በመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታና በጤና ተቋማት ለማስፋፋት በሕዝቡ ለረጅም ጊዜ ይጠየቁ የነበሩ ጥያቄዎችን ለመመለስ ከሕዝብ የሚሰበሰበው ግብር ከፍተኛውን ሚና ይጫወታል ብለዋል።
ያለ ዜጎች ቀጥተኛ ተሳትፎ በሁሉም መስክ የተሳካላትና የተዋጣላት ሀገር መፍጠር አይቻልም ያሉት የጌዴኦ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ሰላማዊ ያሬድ፥ በዞኑ 31 የንግድና ገበያ ማዕከላት ገቢ የማሰባሰብ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ጠቁመው ሁሉም ግብር ከፋይ በግብርና ታክስ አሰባሰቡ ተግባራት ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል ብለዋል።
ዞኑን ለማልማት ካላቸው ፍላጎት ባሻገር የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ኢኮኖሚና ብልጽግናን እውን ማድረግ የሁልጊዜ ራዕያቸው መሆኑን ገልጸው፥ ግብርና ታክስን መሠወር ሀገርን የመካድ ወንጀል በመሆኑ በዘርፉ የሚፈጸሙ አሠራሮችን ሁሉም በመታገል የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅበታልም ብለዋል።
የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ዝናቡ ወልዴ በበኩላቸው በዞኑ ሕብረተሰብ ዘንድ በርካታ የመሠረተ ልማት ፍላጎቶች በመኖራቸው መንግሥት የተቻለውን ሁሉ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረው፥ የመንግሥትን ግብር በታማኝነት በመክፈል ሁሉም ለሀገር ያለውን አጋርነት ማረጋገጥ እንደሚገባ አብራርተዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በግብር አሰባሰብ ላይ የተግባር አንድነት በመፍጠር በዘርፉ የሚፈጸም የገንዘብ ማጭበርበር ወንጀልን ከግለሰቦች ሕይወት ጀምሮ የሀገርንና የሕዝብን ሕልውና የሚጎዳ በመሆኑ ድርጊቱን በሚፈጸሙ አካላት ላይ የማያዳግም ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባም አስረድተዋል።
ዘጋቢ፡ እስራኤል ብርሃኑ – ከፍሰሃገነት ጣቢያችን

More Stories
ህዝቡ የሚያነሳቸውን የፍትህ ጥያቄዎች በአግባቡ ከመመለስ አኳያ የፍትህ ተቋማት የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ አሳሰቡ
ጥራት ያለው፣ ወቅታዊና ተደራሽ የሆነ መረጃ ለህብረተሰቡ በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች ለማድረስ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የሚዛን ቅርንጫፍ ጣቢያ አስታወቀ
የግል እና የጋራ መጸዳጃ ቤቶችን በተገቢው በመጠቀም ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችን አስቀድሞ መከላከል እንደሚገባ በጉራጌ ዞን የእኖር ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት አስገነዘበ