ከ4 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ ላይ ኮረሪማን በማምረት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማደረግ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለጸ

ከ4 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ ላይ ኮረሪማን በማምረት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማደረግ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሰኔ 18/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በቤንች ሸኮ ዞን ደቡብ ቤንች ወረዳ ከ4 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ ላይ ኮረሪማን በማምረት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማደረግ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ የወረዳው ግብርና አካባቢ ጥበቃ ህብረት ስራ ጽፈት ቤት አስታወቀ።

ወረዳው ከቅመማ ቅመም ምርት ባሻገር የተለያዩ ሰብሎች በስፋት የሚመረትበት አከባቢ በመሆኑ የመንገድ መሠረተ ልማቶች ብልሽትና ጥገና በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ተገልጿል።

የደቡብ ቤንች ወረዳ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቡናን ጨምሮ የቅመማ ቅመም ምርቶች በስፋት ከሚያመርቱ አከባቢዎች አንዱና ተጠቃሽ ነው።

ምርቶቹ አርሶ አደሩን በቀላሉ የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ የሚያደረጉ በመሆናቸው ምርታማነቱን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።

በዚህም በወረዳው በጊጪ ክላስተር ኮረሪማ በስፋት የሚመረትበት አከባቢ በመሆኑ በምርቱ ውጤታማ ከሆነው የጊሱ ቀበሌ ወጣት ፍቃዱ ሱርማ ጋር በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት የሚዛን ቅርንጫፍ ጣቢያ ቆይታ አደረጓል።

እንደ ወጣቱ ገለፃ ከዚህ ቀደም በኮረሪማ ምርት ላይ እምብዛም ትኩረት እንደማይሰጡና መንግስት በቅመማ ቅመም ምርት ላይ አፅንኦት በመስጠቱ አመርተው በኪሎ 10 ብር ብቻ ይሸጥ የነበረው ኮረሪማ በአሁን ሰዓት ከ1500 እስከ 2 ሺህ ብር በመሸጡ በትኩረት እያመረተ እንደሚገኝ ተናግሯል።

ወጣት ፍቃዱ ሱርማ በኮረሪማ ምርት በሄክታር 8 ኩንታል በዓመት እስከ 300 ሺህ ብር ገቢ በማገኘት ከገጠር ወደ ከተማ ወጥተው ቤት ሰረቶ ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ገልፀዋል።

ኮረሪማን በባለሙያዎች ድጋፍ በስፋት ቢያመረቱም መንገድ በመበላሸቱ ምክንያት ተጠቃሚ አለመሆናቸውና የሚመለከታቸው አካላትም ምርታቸው የሚያወጡበትን መንገድ በመጠገን መፍትሄ እንዲያበጁላቸውም ወጣቱ ጠይቋል።

በተለይም ኮረሪማ በሄክታር 8 ኩንታል የሚገኝና አንድ ኪሎግራም 2 ሺህ ብር የሚሸጥ ከሆነ ህብረተሰቡ ይህን አውቆ በብዛትና በጥራት በማምረት ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚገባም ገልፀዋል።

በደቡብ ቤንች ወረዳ ከ 4 ሺህ ሄክታር በላይ የኮረሪማ ማሳ ከ70 ሺህ 800 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚገኝ ተጠቁሟል።

በወረዳው በጊጪ ክላስተር ጊሱ፣ ቦጠር ሳይቱ፣ ጋውስና ወፍትን ቀበሌዎች ኮረሪማን በስፋትና በጥራት የሚያመረቱ ቢሆንም ሳይንሳዊና በዘረፉ የሰለጠነ ባለሙያ እንደሚያስፈልጋቸውም ተገልጿል።

በአሁን ሰዓት ክልሉ ለዘረፉ በሰጠው ትኩረት አንድ አርሶ አደር እስከ 300 ሺህ ብር ገቢ የሚያገኝበት ምርት መሆኑን በወረዳው ግብርናና አካባቢ ጥበቃ ህብረት ስራ ጽፈት ቤት የአዝርዕት ሰብሎችና ልማቶች ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ሳቤል ባካሽ አውስተው የዘረፉ ባለሙያዎችን የማሰልጠን ተግባር መጀመሩን ተናገረዋል።

አርሶ አደሮቹ በምርቱ ተጠቃሚ ቢሆኑም በመንገድ መበላሸት ምክንያት ከ300 እስከ 400 ብር አርሶ አደሩን ለትራንስፖር ወጪ እየተዳረገ በመሆኑ መንግስት ለመንገድ መሠረተ ልማት ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ የቡድን መሪው አሰረድተዋል።

የልማት ሁሉ ጀርባ አጥንት የመንገድ መሠረተ ልማት በመሆኑ ከታቀደው 15 ኪ.ሜትር 4 ነጥብ 5 ኪ.ሜትር 3 ወረዳዎችን የሚያገናኝ አዲስ የመንገድ ከፈታ ስራ መሰራቱን የወረዳው ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ጽፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳዊት ለገሰ ገልፀዋል።

ከመንገድ ብልሽትና ጥገና ጋር ተያይዞ እንደአስፈላጊነቱ እየተሰራ እንደሚገኝ ኃላፊው ገልፀው በተለያዩ ምክንያቶች የሚዘጉ ቦዮችን ህብረተሰቡ በመከላከል የመንገድ ደህንነትን ዐቅ እንደሚገባ አስገንዘበዋል።

ዘጋቢ፡ አብዲሳ ዮናስ – ከሚዛን ጣቢያችን