የተገኘውን የሀይማኖት ነፃነት ማስቀጠል የሁሉም ድርሻ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት የኡለማ ምክር ቤት ዋና ሰብሳቢ ሸክ መሀመድ ዘይን ዘይረዲን ተናገሩ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ አራት ዞኖችና የከተማ አስተዳደሮች የዑለማ ምክር ቤቶች በአርባ ምንጭ ከተማ ጉባኤ አካሂደዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ም/ቤት የኡለማ ም/ቤት ዋና ሰብሳቢ ሸክ መሀመድ ዘይን ዘይረዲን፤ እስልምና ተቀባይነትንና ተገቢውን ክብር ያገኘው በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ብቻ መሆኑን አስታውሰዋል።
የሀገሪቱን እድገትና ብልፅግና ለማደናቀፍ ብሎም የሀይማኖትን ነፃነት የሚጋፉ ጉዳዮች ብቅ ብቅ ማለታቸውን ያስታወሱት ሼክ መሀመድ፤ በለውጡ ዘመን የሀይማኖት ነፃነት በአደባባይ የተጠበቀ ስለመሆኑም አንስተዋል።
የእስልምና ም/ቤቶች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ብሎም የመንግስት ጣልቃ ገብነት ተወግዶና የውስጥ አንድነት ወደነበረበት እንዲመለስ መደረጉ የለውጡ ትሩፋት ስለመሆኑም አመላክተዋል።
የቁራንን ሁለንተናዊ ተደራሽነት ለማረጋገጥ በሀገሪቱ ባሉ የተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጉሞ እንዲሰራጭ አለመደረጉን ሼክ መሀመድ እንደተግዳሮት አንስተዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ም/ቤት ፕሬዚዳንት ያሲን ከድር በበኩላቸው፤ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ም/ቤት በአዲስ መልክ መዋቀሩን ተከትሎ በክልሉ ህጋዊ መዋቅር በማደራጀት ስራዎችን እያከናወነ ቆይቷል ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ አያይዘውም አዳዲስና ህጋዊ ሆነው የተደራጁ መዋቅሮችን በመደገፍ በትብብር መሥራት ያስፈልጋል ያሉት ሀጂ ያሲን፤ ኡለማ ም/ቤቶችንም በተደራጀ መልኩ በማዋቀር በአለም ኡለማ ም/ቤቶች መሳተፍ ስለመጀመራቸውም አውስተዋል።
በአርባ ምንጭ ከተማ በተካሄደው የዑለማ ም/ቤት ከወላይታ፣ ከዲላ፣ ከጎፋና ከጂንካ ዞኖች የተውጣጡ የእስልምና እምነት ኡለማዎች፣ ዳኢዎችና ሁስታዞች ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ: በኃይሉ ሙሉጌታ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን

More Stories
የአፈር ጤናን በመጠበቅና ለምነትን በማሻሻል የአርሶ አደሮችን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ምርምር ኢኒስቲትዩት የወራቤ ግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ።
የሕዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ በትኩረት ይሠራል – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)
ጥራቱ የተጠበቀ ከ500 ቶን በላይ እሸት ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ