መንግሥት ለወጣቶች እና ሰው ተኮር ለሆኑ ስራዎች ቅድሚያ በመስጠት መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በትኩረት እንደሚሰራ ገለጸ

ሀዋሳ፡ ሰኔ 15/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) መንግሥት ለወጣቶች እና ሰው ተኮር ለሆኑ ስራዎች ቅድሚያ በመስጠት መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በትኩረት እንደሚሰራ የሀዲያ ዞን አስተዳደር ገለፀ።

“ችልድረንስ ሆፕ ቸስት” የተሰኘ ግብረሰናይ ድርጅት በሀዲያ ዞን ሾኔ ከተማ አስተዳደር ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የወጣቶች ስብዕና ግንባታ እና ቅይጥ የገበያ ማዕከል ለመገንባት የዞኑ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት የመሠረት ድንጋይ አስቀምጧል።

በመረሃ-ግብሩ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የሾኔ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አበራ በዶሬ ከተማዋ በአዲስ መዋቅር ከተቋቋመች አጭር ጊዜ ቢሆንም የህብረተሰቡን የመልማት ጥያቄ ለመመለስ በርካታ ስራዎችን በማከናወን ላይ የሚገኝ ሲሆን በዚህም መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ይህንንም አጋጣሚ በመጠቀም ከተማዋን ለኢንቨስትመንት ምቹ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን በ“ችልድረንስ ሆፕ ቸስት” ድርጅት አማካኝነት የሚገነባው ፕሮጀክት የበርካታ ወጣቶችንና የማህበረሰብን ችግር ለመቅረፍ ሚናው የጎላ መሆኑን አውስተዋል ።

የ“ችልድረንስ ሆፕ ቸስት” ግብረሰናይ ድርጅት በኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር ሚልኪያስ ታየ እንዳሉት ድርጅቱ ላላፉት 14 ዓመታት በኢትዮጵያ 32 ፕሮጀክቶችን በመክፈት በልጆች፣ በወጣቶችና በቤተሰብ ሁለንተናዊ ለውጥ ላይ ሲሰራ ቆይቷል።

በዘላቂ ልማት በልጆችና በወጣቶች ላይ በተሰራው ስራ ከ5ሺህ በላይ ወጣቶች ታግዛው ራሳቸውን ወደ መቻል እንዲደርሱ የተሰራ ሲሆን ከ25ሺህ በላይ የቤተሰብ አባላትን አቅም በማብቃት በራሳቸው ገቢ ማስገኛ የንግድና የተለያዩ ዘርፎች ላይ እንዲሰማሩ ተደርገዋል ነው ያሉት ።

ከትኩረት አከባቢዎች አንዱ በሆነው በሾኔ ከተማ ከ1ዐዐ ሚሊዮን በላይ የሚገነባ የወጣቶች ስብዕና ግንባታና ቅይጥ የገበያ ማዕከል ገንብቶ ለማጠናቀቅ ከስምምነት ላይ መደረሱን ገልፀዋል ።

በዕለቱ የተገኙት የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቴዎስ አንዮ መንግሰት ሰው ተኮር ለሆኑ ፕሮጀክቶች ቅድሚያ በመስጠት የወጣቶች፣ የህፃናትንና የሴቶችን አቅም በሚገነቡና ክህሎታቸውንም በሚያሳድጉ ዘርፎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል ።

በመሆኑም ይህንን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለውን ፕሮጀክት ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጋር በማቀናጀት ለተሻለ ውጤታማነት በትብብር ይሰራል ብለዋል አቶ ማቴዎስ ።

የ”ችልድረንስ ሆፕ ቸስት ” የዓለምአቀፍ ዳይሬክተር እና CEO ሚ/ር ኬን ስፓርክስ ”ወደዚህ የመጣነው ለመለወጥ ራዕይ ስላላችሁ ለውጥ ለማምጣት ነው ፤አዲስ ፕሮጀክት ለመጀመር በመቻላችን ደስታ ይሰማናል፤ይህንን ውብ የሆነ የመስሪያ ቦታ የሰጡ አካላትን አመሰግናለሁ” ብለዋል።

ድርጅቱ ዓለምን ለመቀየር ትክክለኛው መንገድ ለወጣቶች ትኩረት ሰጥቶ መስራት ነው ብሎ ያምናል ያሉት ሚ/ር ኬን ዓለም ላይ ተስፋን መፈንጠቅ ተቀዳሚ የድርጅቱ ተልዕኮ መሆኑን አስገንዝበዋል ።

በዝግጅቱ የሀዲያ ዞን ዋና የመንግሥት ተጠሪ አቶ ሳሙኤል ሽጉጤን ጨምሮ ከፍተኛ የዞንና የከተማ አስተዳደር የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች ፣የሀገር ሽማግሌዎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ወጣቶች እና የማህበረሰብ ክፍሎች በተገኙበት በሁለት ዓመት ውስጥ ተሰርቶ እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቅ መሠረተ ድንጋይ የማስቀመጥ መርኃግብር ተካሄዷል።

ዘጋቢ: ሄኖስ ካሳ – ከሆሳዕና ጣቢያችን