ትምህርት የጠንካራ ሀገር መንግስት ግንባታ ወሳኝ መሳሪያ ነው – ተስፋዬ በልጅጌ(ዶ/ር)
ሀዋሳ፡ ሰኔ 14/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ትምህርት የጠንካራ ሀገር መንግስት ግንባታ ወሳኝ መሳሪያ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የወራቤ ዩኒቨርሲቲ 1 ሺህ 561 ተማሪዎችን በመደበኛ እና በተከታታይ የትምህርት ዘርፎች አስተምሮ አስመርቋል።
በወራቤ ዩኒቨርሲቲ 6ኛ ዙር የተማሪዎች ምረቃ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት በኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ(ዶ/ር)፤ ትምህርት እያንዳንዱ ዜጋ ብቁና ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲገኝ የሚያደርግና የሀገር እድገትና ብልጽግና መሰረት መሆኑን ገልጸዋል።
በሀገር ደረጃ ይህን መነሻ በማድረግ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የትምህርት ዘርፉን ችግሮች ለመፍታት ወሳኝ እርምጃዎች ተወስደዋል ብለዋል ዶ/ር ተስፋዬ።
የትምህርት ጥራት፣ ፍትሃዊነትና ተደራሽነት ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ያነሱት ዶ/ር ተስፋዬ፤ የወራቤ ዩኒቨርሲቲም ከሪፎርሙ መነሻ የተጣለበትን ሀገራዊ ግብ ለማሳካት በስፋት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ፕሮግራሞችን በማደራጀት የመማር ማስተማር ስራውን በማሳለጥ ሀገራዊ ሀላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።
በጥናትና ምርምር ዘርፍ ዩኒቨርሲቲው ከእድሜው የላቀ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑንና በዚህም የዩኒቨርሲቲው መምህራን በጥናትና ምርምር ዘርፍ ያላቸው ተሳትፎና ተነሳሽነት እየጨመረ መጥቷል ብለዋል።
በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ማህበረሰቡ ያለውን ሀብት በተገቢው መጠቀም የሚችልበትን አማራጭ በማሳየት በኩል ተቋሙ የሰራቸው ውጤታማ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አመላክተዋል።
ተመራቂ ተማሪዎች ይህ ምረቃ ጅምር እንጂ ፍጻሜ አለመሆኑን አውቀው ሁልጊዜ ራሳቸውን በማሻሻልና በማስተማር በሀገራቸው ብልጽግና ላይ አሻራቸውን እንዲያኖሩ ዶ/ር ተስፋዬ መክረዋል።
የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ተውፊቅ ጀማል(ዶ/ር) በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ስምንት ዓመታት በመማር ማስተማር፣ በጥናትና ምርም እንዲሁም በማህበረሰብ አገልግሎት ውጤታማ ተግባራት ማከናወኑን አንስተዋል።
ዩኒቨርሲቲው በ2010 ከ1 ሺህ 5 መቶ ባልበለጡ ተማሪዎች፣ በ 4 ኮሌጆች፣ በ14 የትምህርት ክፍሎች ስራ መጀመሩን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ፤ አሁን ላይ በ7 ኮሌጆችና በ47 ዲፓርትመንቶች 47 የመጀመሪያ ዲግሪና 14 የሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራሞችን ከፍቶ ከ10 ሺህ በላይ መደበኛ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ መሆኑን አስረድተዋል።
ዩኒቨርሲቲው ባለፉት 5 ዙር የምረቃ ፕሮግራሞች ከ7 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመጀመሪያ ዲግሪና በሁለተኛ ዲግሪ ማስመረቅ መቻሉን ፕሬዚዳንቱ አንስተዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ከ 1 ሺህ 5 መቶ 61 በላይ ትምህርታቸውን በመደበኛና በተከታታይ መርሃ ግብሮች የተከታተሉ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎች መመረቃቸው ተገልጿል።
ዘጋቢ: ጀማል የሱፍ
More Stories
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ ልዑክ ለወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ሥራና የእርስ በእርስ ግንኙነት ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ታርጫ ከተማ ገቡ
ሴቶች በሁሉም ዘርፍ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው የይርጋጨፌ ወረዳ አስተዳደር አስገነዘበ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የገጠር ትስስርና ተደራሽነት ለምግብ ዋስትና ፕሮግራም በክልሉ 8 ወረዳዎች በመንገድ ግንባታና ጥገና እንዲሁም ተንጠልጣይ ድልድይ፣ የተለያዩ የመንገድ ስትራክቸር ስራዎችን እየሰራ ይገኛል – መሀመድ ኑሪዬ (ዶ/ር)