የከተማውን ሠላም ለማስጠበቅ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የአርባምንጭ ከተማ አሰተዳደር ሠላምና ፀጥታ ጽህፈት ቤት አሰታወቀ

የከተማውን ሠላም ለማስጠበቅ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የአርባምንጭ ከተማ አሰተዳደር ሠላምና ፀጥታ ጽህፈት ቤት አሰታወቀ

የአካባቢያቸውን ሠላም ለማስጠበቅ ከፀጥታ አካላት ጎን በመሆን የበኩላቸውን እየተወጡ መሆናቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ገልፀዋል።

አስተያየታቸውን ከሰጡን የአርባምንጭ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ አብዮት ቶላ እንዳሉት፤ ሠላም ከሁሉም ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን በመረዳት በሥራ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በሠላማዊ መንገድ ተነጋግረው ከመፍታት ባለፈ ለፖሊስ ጥቆማ እንደሚሰጡ ገልፀዋል።

በከተማው በነጭ ሣር ክፍለ ከተማ አግኝተን ያነጋገርናቸው ወ/ሮ እታገኝ ፋንታዬ እና አቶ መሀመድ ሱልጣን አቡበከር እንደተናገሩት፤ ሠላም ከቤት የሚጀምር በመሆኑ ወላጆች ወጣት ልጆቻቸውን በመምከርና በመገሰጽ ጥሩ ስነ-ምግባር ተላበሰው ለአካባቢው ሠላምና ልማት እንዲተጉ በማድረጉ አኳያ ኃላፊነት አለባቸው።

የአርባምንጭ ከተማ አሰተዳደር ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ክበበው አዳል እንደገለፁት፤ ፖሊስ የህብረተሰቡን ደህንነትና ሠላም ከማስጠበቅ ባለፈ በርካታ የልማት አውታሮች በአግባቡ እንዲከናወኑ በሚያስችል መልኩ በቅንጅት እየሰራ በመሆኑ ከተማው አሁን ላይ ሠላማዊ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ኮማንደር ክበበው አዳል ገላፃ፤ አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ንጥቂያ፣ ዝርፊዎች፣ ህገ-ወጥ ንግድንና መሰል ተግባራትን መቆጣጠርና እርምጃዎች በተቀናጀ ሁኔታ እየተወሰዱ በመሆናቸው ለውጥ መምጣቱን ጠቅሰው በህብረተሰቡ ዘንድ አመኔታ የሚያሳጡ ተግባራትን የሚፈፀሙ የፀጥታ አካላትንም በህግ አግባብ ተጠያቂ የማድረግ ሥራ እንደሚሰራ አብራርተዋል።

የአርባምንጭ ከተማ አሰተዳደር ሠላምና ፀጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገበየሁ ፃራ፤ አካባቢው በሠላም ተምሳሌትነት የሚታወቅ በመሆኑ ሠላምን ከማስጠበቅና ከማጽናት ረገድ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከክልልና ከፈዴራል ተቋማት ጋር ሁለንተናዊ ሠላም ለማስፈን በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ኃላፊው አክለውም ህብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጎን በመሆን አጥፊዎችን በማጋለጥ የተለመደውን ትብብር አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።

ዘጋቢ፡ ዓለሚቱ አረጋ – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን