በክልሉ ያሉ የተለያዩ ባህልና የቱሪስት ሥፍራዎችን ለማልማት እና ለማስተዋወቅ እየተከናወነ ያለው እንቅስቃሴ አበረታች መሆኑ ተገለፀ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ በ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ በዝግጅት ምዕራፍ ላይ የሚባክን ጊዜ መኖር የለበትም በሚል ሀሣብ ከዞን እና ልዩ ወረዳ ለተውጣጡ የባህልና ቱሪዝም ሴክተር ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና በሣጃ ከተማ ሰጥቷል።
ሥልጠናውን በንግግር የከፈቱት የየም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሽመልስ እጅጉ፤ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በክልሉ ያሉ የተለያዩ ባህል እና የቱሪስት ሥፍራዎችን ለማልማት እና ለማስተዋወቅ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ አበረታች መሆኑን አስረድተዋል።
የየም ዞን ብርብርሳ ፏፏቴ፣ አንጌሪ ቤተ መንግስት፣ የተለያዩ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ዋሻዎች እንዲሁም አኩሪ ባህላዊ ክዋኔዎች ባለቤት መሆኑን አስገንዝበዋል።
የሳጃ ከተማም የተለያዩ ብሔረሰቦች ተፈቃቅረው የሚኖሩባት ሠላማዊ ከተማ በመሆኗ በቆይታቸው መስህቦቿን እንዲጎበኙም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትልና የባህል ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደግነህ ቦጋለ፤ ቢሮው በ2017 የታቀዱ ሥራዎችን ለማሣለጥ ከ13 በላይ የሕግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት ክትትል እና ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል።
የዚህ ሥልጠና ዓላማም የ2018 ዕቅድ ዝግጅት ምንም ጊዜ ሳይባከን ጠንካራ አቋም ተወስዶ ተግባራትን በውጤታማነት ለመፈፀም አቅም ለመፍጠር ነው ያሉት አቶ ደግነህ፤ ቢሮው በ2018 በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ውስጥ መሪ ለመሆን መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በሴክተሩ የሚከናወኑ ተግባራትን በማወቅ የክልሉን ህዝብ ባህል፣ ታሪክ ቅርስ እና ስነ-ጥበብ እንዲሁም ኪነ ጥበብ ሥራዎችን ወቅቱ በሚፈልገው መልክ ማደራጀት እና መፈፀም አስፈላጊ መሆኑን ነው የተናገሩት።
በሥልጠናው ወቅት የዕቅድ ዝግጅትን በተመለከተ የልማት ዕቅድ ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ካሣ እና የባህል ታሪክ ቋንቋ ኪነ ጥበብ እና የመሰል ጉዳዮችን በተመለከተ ደግሞ ባህል ታሪክ ቅርስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዓለሙ ወንጭሶ አቅርበዋል።
ከሥልጠና ተሣታፊዎች መካከል ጀማል ኡሠን እና ማርታ ፀጋዬ በሰጡት አስተያየት ከሥልጠናው ዕቅድ ዝግጅት እና ከአሠራር ጋር ተያይዞ የሚገጥሙ ችግሮችን ለመፍታት አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል።
የሴክተሩን ሥራ ለማሣለጥ ቢሮው እያደረገ ያለውን ተግባር አጠናክሮ ለማስቀጠል እንሠራለን ብለዋል አስተያየት ሰጪዎቹ።
ዘጋቢ፡ ማሙዬ ፊጣ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
በክልሉ የሚገኙ ነዋሪዎችን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ሥራ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) ገለጹ
የእናቶችንና ጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ በሚደረጉ ጥረቶች ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተገለፀ
የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መስተዳደር (ዶ/ር ) እንዳሻው ጣሰው በተገኙበት በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ምርቃትና የመሰረተ ድንጋይ የማስቀመጥ ስነ-ስረዓት እየተካሄደ ይገኛል