የውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክቶችን አፈጻጸም የቅርብ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ቀሪ ስራዎችን በመለየት ፕሮጀክቶቹን በተያዘላቸው ጊዜ ማጠናቀቅ ያስፈልጋል – ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አንተነህ ፈቃዱ

የውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክቶችን አፈጻጸም የቅርብ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ቀሪ ስራዎችን በመለየት ፕሮጀክቶቹን በተያዘላቸው ጊዜ ማጠናቀቅ ያስፈልጋል – ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አንተነህ ፈቃዱ

የውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክቶችን አፈጻጸም የቅርብ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ቀሪ ስራዎችን በመለየት ፕሮጀክቶቹን በተያዘላቸው ጊዜ ማጠናቀቅ እንደሚያስፈልግ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ ገለጹ።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ በዋን ዋሽ ኘሮግራም የሚከናወኑ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የትምህርትና የጤና ዘርፍ ተግባራትን የባለፈው ዓመት የእስካሁን አፈጻጸምና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድን የሚገመግም የክልሉ ስትሪንግ ኮሚቴ ውይይት በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።

የዋን ዋሽ ኘሮግራም በክልሉ በ21 ወረዳዎችና በሁለት ከተሞች እየተተገበረ ያለ ሲሆን በመንግስትና በተለያዩ ረጂ ድርጅቶች የበጀት ምንጭ በንጹህ ውሃ፣ በትምህርትና ጤና ተቋማት የሳኒቴሽን ስራዎች የሚከናወኑበት ነው።

በንጹህ መጠጥ ውሃ በአምስት አመቱ 170 ሺ ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ የታቀደ ሲሆን አሁን በተደረሰበት 100 ሺ ህዝብ ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ በግምገማ መድረኩ በቀረበው ሰነድ ተገልጿል። በጤናና ትምህርት ተቋማት የተከናወኑ የሳኒቴሽን ስራዎችም አካላዊና ፋይናንሺያል አፈጻጸም ሪፖርት በመድረኩ ቀርቦ ምክክር ተደርጎበታል።

በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመትም 594 ሚሊዮን 333 በላይ በጀት የተመደበ ሲሆን ከ1 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን የሳንቴሽን አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግና ከ170 ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደታቀደ በመድረኩ ተገልጿል።

በቀረበው ዕቅድ ላይ በበጀት አመቱ በገጠርና በከተማ በንጹህ መጠጥ ውሃ፣ በጤናና ትምህርት ተቋማት የሚከናወኑ የውሃና ሳኒቴሽን ስራዎች በዝርዝር ቀርበው አስተያየት ተሰጥቶባቸዋል።

የውይይት መድረኩን የመሩት የስትሪንግ ኮሚቴው ሰብሳቢና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ አንተነ ፈቃዱ፤ የውሃና ሳኒቴሽን የፕሮጀክቶች አፈጻጸም ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች አፈጻጸማቸው በሚፈለገው መጠን ያልሆነው በተለይም የሳጃ እና የወራቤ ከተምች የንጹህ መጠጥ ውሃ ግንባታ የቅርብ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ቀሪ ስራዎችን በመለየት ፕሮጀክቶቹን በተያዘላቸው ጊዜ ማጠናቀቅ ያስፈልጋል ሲሉ አሳስበዋል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት፤ ያለውን ሀብት በአግባቡ በመጠቀም ፕሮጀክቶቹን መፈጸም ይኖርብናል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የዉሃ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ኃይሉ፤ በዋን ዋሽ የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች የተግባርና የበጀት አፈጻጸሙ የተሻለ እንደሆነ አብራርተዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች በተለይም ከኮንትራክተሮች ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ክፍተቶችን የህብረተሰቡን አቅም ጭምር በመጠቀም የቅርብ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ የቀሪ ወራት ተግባራትና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ በተሻለ እንዲፈጸም ይደረጋል ብለዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ፤ በተለይ በሳኒቴሽን ስራዎች ቀሪ ተግባራትን በመገምገም በቀጣይ ዕቅዱ በተሻለ እንዲፈጸም ይደረጋል ብለዋል።

በመድረኩ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሠረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ሀላፊ ዶክተር መሀመድ ኑሪዬ እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት የ2018 በጀት ዓመት የዋን ዋሽ ዕቅድ ጸድቋል።

ዘጋቢ፡ ደመቀ ጀንበሬ – ከወልቂጤ ጣቢያችን