በከተማው አየጨመረ የመጣውን የነዋሪዎች የመልማት ፍላጎት ለማሟላት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ የጎፋ ዞን ላሃ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ

በከተማው አየጨመረ የመጣውን የነዋሪዎች የመልማት ፍላጎት ለማሟላት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ የጎፋ ዞን ላሃ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ

የጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳ ተወላጅ ምሁራን በከተማው እየተገነቡ ያሉ የመሠረተ ልማት ስራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

ከሀገራችን ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ የጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳ ተወላጅ ምሁራን በወረዳውና በላሃ ከተማ አስተዳደር እየተገነቡ ያሉ የመሠረተ ልማት ስራዎችን ተዘዋውረው በጎበኙበት ወቅት በሰጡት አስተያየት በከተማዋ እድገት መደነቃቸውን ገልጸዋል።

ዶ/ር ይስቄል ሳዴቦ ኑሯቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የመሎ ኮዛ ወረዳ ተወላጅ ሲሆኑ ላለፉት 20 ዓመታት ወደ ከተማው ሳይመጡ መቆየታቸውን በመግለጽ፤ በከተማው ውስጥ ለውስጥ ጠጠር መንገድ ግንባታ መሥፋፋት መደሠታቸውን ገልጸዋል።

በህንጻ ግንባታ መሠረተ ልማትና በመብራት ዝርጋታው ዘርፍ ከተማዋ የተሻለ መነቃቃት እንዳሳየች መታዘባቸውን የተናገሩት የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የመጡት አቶ ደመላሽ ኩምሳ ናቸው።

በላሃ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አሸናፊ ጮራ በጉብኝቱ ላይ እንደገለጹት፤ በዚህ አመት በተለያዩ የመሠረተ ልማት ዘርፎች የህዝቡን የመልማት ጥያቄ ለመመለስ አስፈላጊው ጥረት ተደርጓል።

በ19 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ 4.1 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ ጠጠር መንገድ ግንባታ፣ 280 ሜትር የጎርፍ ማፋሰሻ ቦይ ግንባታና 130 ካሬ ሜትር የአደባባይ ግንባታዎች እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።

ከኮሪደር ልማት ጋር በማሥተሳሰር የመንገድ ዳርቻና መሀል የመብራት ዝርጋታ መከናወኑንም ከንቲባው አብራርተዋል።

በከተማው ከ13 በላይ ህንጻዎች በግንባታ ላይ የሚገኙ መሆናቸውም የተገለጸ ሲሆን ከእነዚህም 6ቱ በከተማ አስተዳደሩ ተጀምረው በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኙ የከተማ አስተዳደሩ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ እያሱ ማሩፋ አብራርተዋል።

ተወላጅ ምሁራኑ ከጉብኝታቸው ትዝብት መነሻ አድርገው በከተማው ልማት ዙሪያ የሚቀሩ ጉዳዮችን አንስተው፤ አስፈላጊውን ድጋፍ ከማድረግ ረገድ የምሁራን ድርሻ ዙሪያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በኤሌክትሮ መካኒካል የሙያ ዘርፍ የተሠማሩት ኢንጂነር ዘውዴ ዘለቀ ህብረተሠቡ ለልማት ከሚያደርገው ዘላቂ ድጋፍ ጎን ለጎን በተማሩበት የሥራ መሥክ የከተማውን መንግስት እንደሚያግዙ ቃል ገብተዋል።

ለከተሞች እድገት ከነዋሪዎች የሚሰበሰበው የውስጥ ገቢ ወሳኝ ሚና አለው፡፡ በላሃ ከተማ በየአመቱ የሚሰበሰበው የውስጥ ገቢ ከ10 ሚሊዮ ብር የዘለለ አይደለም። ለዚህም የማዘጋጃ ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ እያሱ የስትራቴጂክ ፕላንና የገቢ ምጣኔ ጥናት ተጠናቆ ወደ ስራ አለመግባትን በምክንያትነት ጠቅሰዋል።

ዘጋቢ: አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን