የአሪ ዞን ሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ መምሪያ የሕፃናትን መብት ለማረጋገጥ የምርጫ ስርዓትን በመከተል ዞናዊ የሕፃናት ፓርላማ ምስረታን በጂንካ ከተማ አካሂዷል።
በዞናዊ የሕፃናት ፖርላማ መረጣ መርሃ ግብር የምርጫ ስርዓትን ተከትሎ ተማሪ ጦይባ ዑሜር ከደቡብ አሪ ወረዳ ዋና አፈ ጉባኤ፣ ተማሪ ቢንያም አዱኛ ከጂንካ ከተማ አስተዳደር ምክትል አፈ ጉባኤ፣ ተማሪ ይስሐቅ ቦጋለ ከዎባ አሪ ወረዳ ፀሐፊ እንዲሁም በቋሚ ኮሚቴነት የሚያገለግሉ ሌሎች አባላትንም መርጠዋል።
የተመረጡ የሕፃናት ፓርላማ አባላት የተጣለባቸውን ኃላፊነት በታማኝነትና በቅንነት ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
እስከታችኛው መዋቅር የሕፃናት ፓርላማ አደረጃጀትን በማጠናከር የሕፃናት መብትና ደህንነትን ለማረጋገጥ እንደሚሠሩ አዲስ የተመረጡት የአሪ ዞን የሕፃናት ፓርላማ ዋና አፈ ጉባኤ ተማሪ ጦይባ ዑሜር ገልፀዋል።
በሕፃናት ላይ የሚደርሱ አካላዊና ስነልቦናዊ ጉዳቶችን ለማስቀረትና መብታቸውን ለማስከበር የሕፃናት ፓርላማን ማቋቋም ሚናው የላቀ ነው ያሉት በመምሪያው የሕፃናት መብትና ደህንነት ማስከበር ሥራ ሂደት ቡድን መሪ ወይዘሪት እቴቴ አያለው ናቸው።
የአሪ ዞን ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ርብቃ አለማየሁ እንደገለፁት፤ ከዚህ በፊት ያገለገሉ አባላትን በአዲስ ለመተካትና ለማጠናከር በኢፌዲሪ ህገመንግስት አንቀፅ 36 መሠረት የሕፃናት ፓርላማው መደራጀቱን አስረድተዋል።
ኃላፊዋ አክለው የሕፃናትን ሁለንተናዊ ተሣታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሕፃናት ፓርላማ አመራርነት የተመረጡ በቁርጠኝነትና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመናበብ እንዲሠሩም አሳስበዋል።
ዘጋቢ፡ ተመስገን አሰፋ – ከጂንካ ጣቢያችን

More Stories
ዲግሪው “ወረቀት ብቻ ሳይሆን፣ የሀገር ተስፋና የትውልድ ኃላፊነት ነው” – አፈወርቅ ካሱ (ፕ/ር)
በክልሉ የተጀመሩ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ የድጋፍና ክትትል ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ ገለጹ
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርናና ገጠር ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሀላባ ቁሊቶ ከተማ የግብርና ስራዎችን ተመለከተ