ሀዋሳ፡ ሰኔ 13/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የአካባቢ ጽዳትን ባህል ማድረግ የሥልጣኔ ምልክት መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ደን አካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡
የዘንድሮው ጽዱ ኢትዮጵያን ባህል የማድረግ ንቅናቄ “የፕላስቲክ ብክለትን እንግታ” በሚል መሪ ቃል በአገር አቀፍ ደረጃ ለ32ኛ ጊዜ እንዲሁም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለ2ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደን አካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቴ ጊጄ፤ የአካባቢ ብክለት በዓለም አቀፍ ደረጃ ስጋት እየሆነ መምጣቱን አውስተው ዘንድሮ ጽዱ ኢትዮጵያን ባህል የማድረግ ንቅናቄ በአገር አቀፍ ደረጃ ለ32ኛ ጊዜ እንዲሁም በክልሉ ለ2ኛ ጊዜ እየተከበረ ነው ብለዋል።
ንቅናቄው በክልሉ ለተከታታይ ስድስት ወራት የሚቆይ ሲሆን በዚህም የፕላስቲክ፣ የአፈርና የውሃ እንዲሁም የአየርና የድምፅ ብክለትን የመግታት ሥራ በትኩረት የሚሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
የቆሻሻ አወጋገድና ፅዳት ዙሪያ ሁሉም ህብረተሰብ ተሳታፊ እንዲሆን የማድረግና ለአካባቢ ጥበቃና ፅዳት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና የመስጠት መርሐ ግብርም ይከናወናል ያሉት አቶ ግዛቴ፤ የቆሻሻ አወጋገድ ተግባራትን በማስመልከት የወጡ አዋጆችን የማስከበር ሥራ ላይ ትኩረት ይሰጣል ብለዋል።
አክለውም ጽዳት ባህል ማድረግ የሥልጣኔ ምልክት ነው ያሉት ኃላፊው፤ የአካባቢ ንፅህና የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ሁሉም ሰው ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል።
በኢፌዲሪ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ እንደገለፁት፤ ጽዱ ኢትዮጵያን ባህል የማድረግ ንቅናቄ በፌደራል ደረጃ ከግንቦት ወር ጀምሮ እየተካሄደ ሲሆን በገጽ ለገጽ ከ15 ሚሊየን ህዝብ በላይ እንዲሁም በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች ለ50 ሚሊየን የህብረተሰብ ክፍሎች የግንዛቤ ትምህርት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው።
በክልሉ በተጀመረው የንቅናቄ መርሀ ግብር የከተማ ፅዳትና የችግኝ ተከላ መርሀ-ግብር የተከናወነ ሲሆን የፓናል ውይይትም ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።
ዘጋቢ: አስናቀ ካንኮ – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን
More Stories
እመርታ ለዘላቂ ከፍታ!
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የእምርታ ቀንን በማስመልከት ያስተላለፉት መልዕክት:-
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) መልዕክት፡-