ስፖርት የወንድማማችነት እና የልማት መጠናከር አንዱ ማሳያ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ

ስፖርት የወንድማማችነት እና የልማት መጠናከር አንዱ ማሳያ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ

6ኛው የመላው ኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ሻምፒዮና የችቦ ቅብብል መርሃ ግብር በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የም ዞን በሳጃ ከተማ በደማቅ ሁኔታ ተካሂዷል።

የሳጃ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ጌታሁን ካሣሁን በዚህ ወቅት ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር፤ የየም ዞን የተለያዩ ባህላዊ እሴቶች እና የቱሪስት መስህቦች መገኛ መሆኑን ተናግረዋል።

የየም ዞን ካሉት አኩሪ ባህላዊ እሴቶች መካከል ስርቆት፣ የሴት ልጅ ግርዛት፣ ልመና እና የመሳሰሉት ውግዝ መሆናቸውን በመጠቆም ዞኑ የአትሌት ብርቱካን ወልዴ መገኛ መሆኑንም አክለዋል።

የሳጃ ከተማ በእንግዳ ተቀባይነቷ ትታወቃለች ያሉት ከንቲባው፤ በተለያዩ ስፖርቶች ላይ ከተሠራ እንደ ብርቱካን ሀገርን የሚያኮሩ ስፖርተኞች ይፈልቃሉ ብለዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ምክትልና የስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሠይፈ ዓለሙ በበኩላቸው፤ ስፖርት የሠላም፣ የፍቅር፣ የመቻቻል እና የአብሮነት ተምሣሌት ነው ብለዋል።

ይህን አብሮነት፣ አንድነት እና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር የሚፈጥረውን ስፖርት ይበልጥ ለማጉላት በተለያዩ የክልል ከተሞች አቀባበል እየተደረገ ሳጃ ከተማ መድረሱን ተናግረዋል።

በከተማው በተካሄደው የአቀባበል ስነሥርዓት መደሰታቸውን የተናገሩት አቶ ሠይፈ፤ ይህም ስፖርት የወንድማማችነት እና የልማት መሠረት መሆኑ አንዱ ማሣያ ነው ብለዋል።

የኢፌዲሪ ባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ችቦ ቅብብሎሽ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሽታዬ ገዛኸኝ፤ በሳጃ ከተማ የተደረገው አቀባበል ከምንም በላይ እንግዳ ተቀባይ ሕዝብ ያለበት ከተማ መሆኑን የሚያመላክት ትዕይንት ነው ብለዋል።

የየም ዞን የባህላዊ መድኃኒት፣ ኪነ ጥበብ እና ልዩ ልዩ አኩሪ ታሪክ እንዳለው በመጥቀስ በመሆኑም በቀጣይ የተለያዩ ውድድሮችን በማዘጋጀት የስፖርተኞች መፍለቂያ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በከተማውና አካባቢው ህዝብ ለተደረገው ደማቅ አቀባበልም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች ለ9 ዓመታት ተቋርጦ የቆየው መላው የኢትዮጵያ ጨወታዎች ዘንድሮ ከነገ ሰኔ 10/2017 ዓ.ም ጀምሮ በጅማ ከተማ እንደሚደረግ የኢፌዲሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

ዘጋቢ፡ ማሙዬ ፊጣ – ከወልቂጤ ጣቢያችን