በመላው ሀገሪቱ በቀጣይ ጊዜያት 50 ሞዴል ትምህርት ቤቶች ለመገንባት እየተሰራ ነው መሆኑን የኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስትር ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር) ገለጹ
የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር) እና ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አንተነህ ፍቃዱ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በዱራሜ ከተማ በ509 ሚሊየን ብር የሚገነባውን ሞዴል ትምህርት ቤት ግንባታ አስጀምረዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ በሀገሪቱ አሁን ላይ 31 ሞዴል ትምህርት ቤቶች ለመገንባት እየተሰራ ነው።
በዱራሜ ከተማ በ509 ሚሊየን ብር የሚገነባው ሞዴል 2ኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት የዚሁ አካል ስለመሆኑ ሚኒስትሩ አብራርተዋል። በቀጣይ ቁጥሩን 50 የማድረስ እቅድ እንዳለም አብራርተዋል።
ሞዴል ትምህርት ቤቱ አጠቃላይ መሰረተ ልማት እንደሚሟሉለት የገለጹት ሚኒስትሩ ፣ቤተ ሙከራዎች፣የመዝናኛ ስፍራዎች፣ የቴክኒክና ሙያ መማሪያ እና ሌሎችንም እንደሚያሟላ ጠቁመዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክል ርዕሰ መስተዳድር፣የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ በበኩላቸው፤ በሀገሪቱ የተካሔደውን የትምህርት ማሻሻያ ፖሊሲን ተከትሎ በዘርፋ በርካታ ስራዎችን ተግባራዊ መደረጉን ተናግረዋል።
በአዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ የፈተና አስተዳደር ስርዓት ላይ ለውጥ መደረጉን ተከትሎ በ8ኛ እና በ12ኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተና የሚያልፉ ተማሪዎች ቁጥር ዝቅተኛ መሆኑን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል።
በክልሉ የትምህርት ጥራት የማስጠበቅ ስራ ልዩ ትኩረት እንደተሰጠውም አቶ አንተነህ ጠቁመዋል።
ለትምህርት ጥራት መጠበቅ በዋነኛነት ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ቤት ወሳኝ ነው ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ዘርፉን ለማጎልበት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በክልሉ ደረጃቸውን ያሟሉ ትምህርት ቤቶች ከ48 በመቶ በላይ እንዳልሆነ የተናገሩት አቶ አንተነህ በ1ኛ እና በመካከለኛ ደረጃ ደግሞ 19 በመቶ ብቻ ደረጃቸውን ስለማሟላታቸው ጠቁመዋል።
እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል ትምህርት ቤቶቻችን ያሉበት ደረጃ ታውቆ የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ተግባራዊ እየተደረገ ስለመሆኑ አቶ አንተነህ አብራርተዋል።
በክልሉ በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።
በዛሬው እለት ግንባታው የተጀመረው ሞዴል ትምህርት ቤት ለሌሎች ትምህርት ቤቶች ለተሞክሮነት የሚበቃ ስለመሆኑም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
የከምባታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አረጋ እሸቱ እንደገለጹት በዞኑ የትምህርት ስብራትን ለመጠገን ዘርፈ ብዙ ስራዎች ተግባራዊ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ለቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ልዩ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው በዞኑ ግንባታው የተጀመረው ሞዴል ትምህርት ቤት በትምህርት ጥራት እና በተማሪዎች ውጤት መሻሻል ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።
ዘጋቢ: ወንድወሰን ሽመልስ
More Stories
በክልሉ ለተገኘው ሰላምና ልማት የታማኝ ግብር ከፋዮች ሚና የላቀ መሆኑን የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለፁ
የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ የሱፐርቪዥን ልዑካን ቡድን በሀላባ ቁሊቶ የከተማ ልማት ስራዎችን ጎብኝቷል
ተወዳዳሪ ዜጋ እንድትሆኑ ሳትሰርቁ ጠንክራችሁ ፈተናችሁን በራሳችሁ ሥሩ – ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር)