በቀቤና ልዩ ወረዳ ማህበረሰቡ በመንገድ መሰረተ ልማት ስራ እያደረገ ያለው ተሳትፎ የሚበረታታ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት – የልዩ ወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞሳ ኢዶሳ
ሀዋሳ፡ ሰኔ 05/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በቀቤና ልዩ ወረዳ ማህበረሰቡ በመንገድ መሰረተ ልማት ስራ እያደረገ ያለው ተሳትፎ የሚበረታታ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የልዩ ወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞሳ ኢዶሳ ገለፁ፡፡
በልዩ ወረዳው በ3 ቀበሌያት በማህበረሰቡና በመንግስት ተሳትፎ በ10 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የ8 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል፡፡
የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞሳ ኢዶሳ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ በልዩ ወረዳው በማህበረሰቡና በመንግስት ተሳትፎ በርካታ የመንገድ መሰረተ ልማት ስራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡
በተለይም በልዩ ወረዳው ማህበረሰቡ በመንገድ ልማት ስራ እያደረገ ያለው ድጋፍና ተሳትፎ የሚበረታታ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስረድተዋል፡፡
የቀቤና ልዩ ወረዳ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ኸይረዲን ሽኩር በበኩላቸው፤ በተያዘው በጀት አመት በልዩ ወረዳው የ30 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ግንባታ በማህበረሰቡና በመንግስት ተሳትፎ ለማከናወን ግብ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
በዚህም እስካአሁን ከማህበረሰቡ 20 ሚሊየን ብር በመሰብሰብ ለመንገድ መሰረተ ልማት ማዋል ተችሏልም ነው ያሉት፡፡
በዕለቱ በልዩ ወረዳው በደቀንሺሞላ፣ በገርባጃና በፍቃዶ ቀበሌያት በማህበረሰቡና በመንግስት ተሳትፎ ግንባታቸው ተጠናቆ የተመረቁ 3 የጠጠር መንገድ ፕሮጀክቶች 8 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር እንደሚሸፍኑና 10.5 ሚሊየን ብር ወጪ መደረጉን አስረድተዋል፡፡
አቶ ናስር አህመድ፣ ወ/ሮ ሙኒራ መሀመድና ወጣት ማህሙድ አለሙ በልዩ ወረዳው የገርባጃና የደቀንሺሞላ ቀበሌያት ነዎሪዎች ናቸው፡፡
በሰጡት አስተያየትም ከዚህ ቀደም በቀበሌያቱ የመንገድ መሰረተ ልማት ባለመኖሩ ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች ተጋልጠው መቆየታቸውን አስታውሰው አሁን ላይ በቀበሌያቸው የጠጠር መንገድ ግንባታ ተከናውኖ መመረቅ በመቻሉ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡
በግንባታውም የበኩላቸውን ድጋፍና ተሳትፎ ማድረጋቸውን የገለፁት ነዋሪዎቹ መንገዶቹ ዘላቂ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ አስፈላጊውን ጥበቃና እንክብካቤ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ጅላሉ ፈድሉ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
በክልሉ ለተገኘው ሰላምና ልማት የታማኝ ግብር ከፋዮች ሚና የላቀ መሆኑን የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለፁ
የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ የሱፐርቪዥን ልዑካን ቡድን በሀላባ ቁሊቶ የከተማ ልማት ስራዎችን ጎብኝቷል
በመላው ሀገሪቱ በቀጣይ ጊዜያት 50 ሞዴል ትምህርት ቤቶች ለመገንባት እየተሰራ ነው መሆኑን የኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስትር ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር) ገለጹ