የመንገድ መሰረተ ልማት ጥያቄን ለመመለስ ማህበረሰቡን ያሳተፈ ስራ እየተሰራ መሆኑን በጎፋ ዞን ቡልቂ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ
በከተማው እየተሰራ ባለው የመንገድና የዲች መሰረተ ልማት ስራ በመሳተፍ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን በከተማው ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የቡልቂ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሲሳይ ፍሬው እንደተናገሩት፤ የከተማውን ህዝብ የመሰረተ ልማት ጥያቄ ለመፍታት በመንግስትና በማህበረሰብ ተሳትፎ በከተማው ባሉ በሁሉም ቀጠናዎች የመንገድ ከፈታ፣ የአፈር እና ጠጠር የማልበስ እንዲሁም የመጠገን ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በተያዘው በጀት አመት በማህበረሰብ ጉልበትና በማቺንግ ፈንድ ገንዘብ ድጋፍ 4.7 ኪሎ ሜትር መንገድና ዲች እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለዚህ ስራ ውጤታማነት የማህበረሰቡ ድጋፍ ትልቅ አበርክቶ እንደነበረው የተናገሩት አቶ ሲሳይ፤ በከተማው በተለያዩ ቀጠናዎች የመንገድ ከፈታ፣ ጠጠር የማልበስ ስራ እና ዲች ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
የመንገድ መሰረተ ልማት ስራውን ውጤታማ ለማድረግ ከ3 ሚሊየን ብር የማህበረሰብ ጉልበትን ጨምሮ በተሰራው ስራ የመንገድ መሰረተ ልማትን ተደራሽ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን የቡልቂ ከተማ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ኃላፊ ተወካይና የማስፈፀም ዘርፍ ኃላፊ አቶ አየለ አማን ገልፀዋል።
አሁን ላይ የተሰሩና እየተሰሩ ያሉ መንገዶችም ዘላቂነት ያለውን አገልግሎት እንዲሰጡ የተጠናከረ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ ነው ያሉት አቶ አየለ፤ በቀጣይም በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በከተማው በተለያዩ ቀጠናዎች በመንግስትና በማህበረሰብ ተሳትፎ እየተሰራ ያለው የመንገድ መሰረተ ልማት ዘላቂነት ያለው እንዲሆን ጥራቱን የጠበቀ የግንባታ ስራ እየተከናወነ መሆኑን የገለፁት በከተማው የህብረተሰብ ተሳትፎ አስተባባሪዎች አቶ ደባልቄ ደጀኔ እና በቀለ ጎሳ ናቸው።
በተለያዩ ማህበራት ከተደራጁ ወጣቶች መካከል አቶ ታዬ ደለሌ እና መ/ር አስራት መንገሻ በሰጡት አስተያየት፤ ቡልቂ ከተማ በእድሜዋ ልክ ያላደገችና በሁሉም አካባቢዎች የመንገድ መሰረት ልማት ተደራሽ ባለመሆኑ ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሲዳረጉ መቆየታቸውን ተናግረው በአሁን ወቅት ከተማው የማህበረሰቡን የመንገድ መሰረት ልማት ተደራሽነት ጥያቄ ለመፍታት በሚሰራው ስራ በርካታ የስራ ዕድል በመፈጠሩ በጉልበት፣ በሙያና በገንዘብ በማገዝ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ተናግረው አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ: ድጋፌ ድክሬ – ከሳውላ ጣቢያችን
More Stories
በቀቤና ልዩ ወረዳ ማህበረሰቡ በመንገድ መሰረተ ልማት ስራ እያደረገ ያለው ተሳትፎ የሚበረታታ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት – የልዩ ወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞሳ ኢዶሳ
የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ከ”ኤስ ኦ ኤስ የህፃናት መንደር” ሀዋሳ ቅርንጫፍ ጋር በመተባበር በሀዲያ ለአምብቾ ጎዴ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተለያዩ የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ
በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳሰበ