የየም ብሔረሰብ ሀገር በቀል የመድሃኒት ለቀማና ቅመማን በጥናት በመደገፍ ሰንዶ ለማስቀመጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢፌዴሪ ባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ገለፀ።
“ሀገር በቀል ዕውቀቶች እና ባህላዊ እሴቶች ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል በየም ብሔረሰብ ባህላዊ መድኃኒት ለቀማና ቅመማ ዕውቀት ላይ የተካሄደ የጥናት ውጤት ላይ የግምገማ መድረክ በሳጃ ከተማ ተካሄዷል።
መድረኩ የኢፌዴሪ ባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ስለመሆኑም ተመላክቷል።
የኢፌዳሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የባህል እና ቋንቋ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ ሮ ነፊሳ አብዱልማዲ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የየም ብሔረሰብ ሀገር በቀል የመድሃኒት ለቀማና ቅመማን ለዘመናት ጠብቆ በማቆየት ትውልድ ተሻጋሪ እንዲሆን እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል።
በተለይም ብሔረሰቡ በዘመናዊ ሕክምና መድሃኒት ያልተገኘላቸው እንዲሁም ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ በሽታዎችን በባሕላዊ መንገድ በማከም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያበረክት መቆየቱን አውስተዋል።
ይህንን የብሔረሰቡን ባህላዊ መድሃኒት ለቀማ እሴት በጥናት በተደገፈ መልኩ ሠንዶ ለማቆየት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ነው የገለፁት።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትልና የባህል ዘርፍ ሀላፊ አቶ ደግነህ ቦጋለ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ባሕላዊ ሀገር በቀል ዕውቀቶች እና እሴቶችን ለማበልፀግ ከጥናት እና ምርምር ተቋማት ጋር እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል።
በበጀት ዓመቱ የየም ብሔረሰብ ባህላዊ መዲሃኒት ለቀማና ቅመማ ሥርዓት “ሳሞ ኤታ” ከኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር መጠናቱን ተናግረዋል።
በተለይም በየም ብሔረሰብ የሴት ልጅ ግርዛት እና ልመና የተወገዘ በመሆኑ እነዚህን እና የመሣሠሉ እሴቶችን ጠብቆ ማቆየት ተገቢ በመሆኑ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት ብለዋል ።
የየም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሽመልስ እጅጉ በኩላቸው ዞኑ የበርካታ አኩሪ ባህላዊ እሴቶች እንዲሁም በሽታዎችን የሚያክሙበት የሀገር በቀል መድሃኒት ዕውቀት ባለቤት መሆኑን ተናግረዋል።
በዞኑ የመድሃኒት ለቀማ ቀንና ወር ተቆርጦለት እንደሚከናወን በማንሳት በየዓመቱ ከ210 በላይ ዕፀዋት ቅጠል፣ ቅርፊት እና ስራስር ተለቅሞ ለሰው እና እንስሣት መድኃኒትነት እንደሚውል ገልፀዋል።
ይህንኑ የብሔረሰቡን ባሕላዊ ሀገር በቀል ዕውቀት በተደራጀ መልኩ ለማስቀጠል እየተሠራ ያለው ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ዋና አስተዳዳሪው አስታውቀዋል።
በመድረኩ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት በኢፌዴሪ ባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የጥናት ቡድን መሪ አቶ ማስረሻ አበበ በየም ብሔረሰብ ዘንድ የሚከናወነው ባህላዊ የመዲሃኒት ለቀማ ከ50 በላይ በሽታዎችን እንደሚፈውስ ገልፀዋል።
መድኃኒት ለቀማው እና ቅመማው በዓለም ላይ ካሉ ግኝቶች በዓይነቱ ልዩ በሆነ መልኩ የሚከናወን ነው ያሉት ጥናት አቅራቢው ይህንኑ ዘርፍ በማሣደግ ኢኮኖሚያዊ ልማት ላይ ማዋል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በመሆኑም ለዘርፉ ውጤታማነት ባለድርሻ አካላት ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ተናግረዋል ።
በመድረኩ ላይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብሄረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አቡቶ አኒቶን ጨምሮ የክልል እና የዞን ክፍተኛ የመንግስት የሥራ ሀላፊዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፣ ማሙዬ ፊጣ-ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
በጤና ዘርፍ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት ብቁ የሰው ሀይል ወሳኝ ሚና እንዳለው የጤና ሚኒስቴር ገለጸ
በሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ግብርና ጽ/ቤት በክላስተር የቡና ችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ መርሀ-ግብር ተካሄደ
በሲዳማ ክልል በዶሮ ዕርባታ ስራ ውጤት ታይቷል አለ የክልሉ እንስሳት ሃብት ልማት ቢሮ