የጋልማ ከተማ አስተዳደር ምስረታ ተካሄደ
ሀዋሳ: ሰኔ 01/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጎፋ ዞን ዛላ ወረዳ የጋልማ ከተማ አስተዳደር የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ምስረታውን አከናውኗል።
በከተማ አስተዳደር ዕውቅና አሰጣጥ ስነ ስርዓቱ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የዛላ ወረዳ ዋና አሰተዳዳሪ አቶ ያዕቆብ ዘካሪያስ ወረዳው በርካታ የግብርናና ማዕድን ምርት ዕምቅ አቅም ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
ተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሐብቶችን በአግባቡ በመጠቀም ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደረጉ በርካታ የመሠረተ ልማት አውታሮች እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል ።
ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ እያስመዘገበ ያለውን ከተማ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስና በግብርና ምርት እምርታዊ ለውጥ ለማምጣት ጋልማ በፈርጅ 3 ከተማነት ዕውቅና ማግኘቱ የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አቶ ያዕቆብ አሰረድተዋል።
የጎፋ ዞን ዋና አስተዳደሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ በበኩላቸው የከተማውን ህዝብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ የሥራ ዕድል ለመፍጠር በውስጧ የሚገኙ የተፈጥሮ ፀጋዋን በመጠቀም ማልማት እንደሚቻል ተናግረው ወጣቶች አምራች ዜጋ በመሆን ተፈጥሮ የሰጠውን ሀብት በአግባቡ በመጠቀም ጋልማ ከተማን እንዲያለሙ መልዕክታቸውን አሰተላልፈዋል ፡፡
በምክትል ርዕስ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ አባተ በኩላቸው የከተሞች የደረጃ ለውጥ የተቀላጠፈ መንግሰታዊ አገልግሎት ለህብረተሰቡ ከመስጠት ባለፈ መሠረተ ልማት ዝርጋታን ተደራሽ በማድረግ አካባቢው በይበልጥ የሚታወቅበትን የበቆሎና አርቲ ሰብሎችን እንዲሁም ሰንጋ በሬ ምርትን በዓለም ገበያ ለማሰተዋወቅ የክልሉ መንግስት አሰፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል ፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት የከተማና መሠረት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ፤ ዜጎች በተሟላ መሠረት ልማት በጋራ እንዲኖሩ ከተሜነት አሰፈላጊ በመሆኑ በክልሉ 29 በመቶ የሚሆኑ ህብረተሰብ ክፍሎች በከተማ እንደሚኖሩ ጠቅሰው በቀጣይ 40 በመቶ ለማድረስ በትኩረት እንደሚሰራ ገልፀዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊና የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ገ/መስቀል ጫላ ከተሞች በርካታ መሠረተ ልማት የሚያገኙበት የዕደገት ማዕከል በመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የተሰጠውን ከተማን የማልማት ተግባር በአግባቡ እንዲወጡ መልዕክታቸውን አሰተላልፈዋል፡፡
የከተማው ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት ከተማው ወደ ፈርጅ 3 በማደጉ መደሰታቸውን ገልፀው ከተማው ወደተሻለ ደረጃ ለማሳደግ ለሰላም ዘብ በመሆንና በልማቱ ረገድ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል ።
ዘጋቢ፡ ስንታየሁ ሙላቱ – ከሳውላ ጣቢያችን

More Stories
በክልሉ የሚገኙ ነዋሪዎችን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ሥራ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) ገለጹ
የእናቶችንና ጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ በሚደረጉ ጥረቶች ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተገለፀ
የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መስተዳደር (ዶ/ር ) እንዳሻው ጣሰው በተገኙበት በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ምርቃትና የመሰረተ ድንጋይ የማስቀመጥ ስነ-ስረዓት እየተካሄደ ይገኛል