በቅርቡ በሚሰጠው የ6ኛ እና የ8ኛ ክልላዊ ፈተና ላይ ከ53 ሺህ በላይ ተማሪዎች ለፈተና እንደሚቀርቡ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሀዲያ ዞን ትምህርት መመሪያ አስታወቀ
በ2017 የትምህርት ዘመን የ6ኛ እና የ8ኛ ክልላዊ ፈተናዎች ማስፈፀሚያ ዕቅድ ላይ የተደረገ ዞን አቀፍ ኦሬንቴሽን መድረክ ተካሂዷል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የሀዲያ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የትምህርት መምሪያ ኃላፊ ዶ/ር በፈቃዱ ገ/ሃና፤ ትምህርት ትውለድ የማስቀጠል ጉዳይ በመሆኑ በሀገሪቱ ትኩረት ተሰጥቶ ከሚተገበርባቸው ጉዳዮች መካከል የፈተናና የምዘና ጉዳይ ተጠቃሽ ነው ብለዋል።
በመሆኑም በፈተና ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን አሰቀድሞ መከላከል ተፈታኞችን በስነ-ልቦና ማጠናከር በፈተና ወቅት የፀጥታ ጉዳይ በጥብቅ ስነ-ምግባር መመራት እንደሚገባ ምክትል አስተዳዳሪው አስገንዝበዋል።
በተለይም እንደ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሰጠው የ6ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና የሚወስዱ በዕድሜያቸው ህፃናት በመሆናቸው ልዩ ትኩረት መስጠትና ከስነ-ልቦና ጫና መከላከል ያስፈልጋል ሲሉ ዶ/ር በፈቃዱ መክረዋል።
በራሱ ሰርቶ የሚያልፍ ተማሪ መፍጠር ይገባል ያሉት ኃላፊው ሊሰራጩ የሚችሉ ሀሰተኛ ውዥንብሮችን በመከላከል ኩራጃን አስቀድሞ መከላከል እንደሚገባ ገልፀዋል።
በመድረኩ የውይይት ሰነድ ያቀረቡት በመምሪያው የፈተና ምዘና ቡድን መሪ አቶ አድነው አቢዮ፤ በ2016 የትምህርት ዘመን በጠንካራና በጉድለት የታዩ ጉዳዮችን አንስተዋል።
በተለይም ማህበረሰቡ ስለኩራጃ ያለው አመለካከት ውስንነት፣ የሎጂስቲክ እጥረት፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የቁርጠኝነት ማነስ እና አለመናበቦች እንዳጋጠሙ ጠቁመዋል።
በመሆኑን ፈተናው በተዘጋጁ ትምህርት ቤቶች በክላስተር የሚሰጥ በመሆኑ የፀጥታ እና የፈተና ግብረ-ሃይል በመናበብ እና በዲስፕሊን መምራት ተገቢነት እንዳለው ተናግረዋል።
ተፈታኞች ከሀሰተኛ መረጃዎች ራሳቸውን በማራቅ እንደ ኤሌክትሮኒክስ ያሉ የተከለከሉ ነገሮችን ባለመያዝ እና ለህግና ደንብ ተገዥ በመሆን ፈተናው በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
በውይይት መድረኩ በዞኑ ከሚገኙ ከ20 መዋቅሮች የተውጣጡ የትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ የፖሊስ እና የፀጥታ ዘርፍ አስተባባሪዎች፣ የፈተና ቡድን መሪዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በዞኑ በቅርቡ በሚሰጠው ክልላዊ ፈተና ላይ ከ6ኛ ክፍል 25 ሺህ 803 ከ8ኛ ክፍል ደግሞ ከ27 ሺህ 198 ተማሪዎች ለፈተና እንደሚቀመጡ ተገልጿል።
ዘጋቢ፡ ሄኖስ ካሳ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የኢፌዲሪ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት ከ82 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ በጉራጌ ዞን ምሁር አክሊል ወረዳ መቆርቆር ቀበሌ ያስገነባው የንጹህ መጠ ውሃ ፕሮጀክት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ
የኡዱሂያ የዕርድ ስርዓት….የአብሮነት ነፀብራቅ
“የብልጽግና ጉዞአችንና የንግዱ ማህበረሰብ ሚና” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ ክልላዊ የንግዱ ማሕበረሰብ ማጠቃለያ የውይይት መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው