ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ እየተደረገ ባለዉ ጥረት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍና ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ

ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ እየተደረገ ባለዉ ጥረት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍና ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ግንቦት 22/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ እየተደረገ ባለዉ ጥረት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍና ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የጉራጌ ዞን ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ገለፀ።

“የአካል ጉዳተኞች የመሪነት ሚና በማጉላት አካታችና ዘላቂ ልማትን እናረጋግጥ!” በሚል መሪ ቃል በሀገራችን ለ32ኛ በአለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ33ኛ ጊዜ የሚከበረው የአካል ጉዳተኞች ቀን በዓል በአገና ከተማ ተከብሯል።

በበዓሉ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የጉራጌ ዞን ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች መምሪያ ሀላፊ አቶ መኩሪያ ተመስገን እንደገለፁት፤ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ እየተደረገ ባለዉ ጥረት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚና የጎላ ነው።

አካል ጉዳተኝነት በማንኛውም ሰው ላይ ሊፈጠር እንደሚችል የገለፁት አቶ መኩሪያ፤ በሀገሪቱ 17 ነጥብ 6 በመቶ የሚሆነው ህዝብ አካል ጉዳተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመሆኑም ሁሉም ማህበረሰብ እነዚህን አካላት በመደገፍ አለኝታነቱን ማሳየት እንዳለበት አሰረድተዋል።

በዞኑ የሚገኙ አካል ጉዳተኞች በማህበር ተደራጅተው እንዲጠቀሙ በመምሪያው አማካኝነት ከ6 መቶ ሺህ ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን የተናገሩት አቶ መኩሪያ፤ በቀጣይም በዘርፉ የወጡ አዋጆችና ደንቦችን በማሻሻል ይበልጥ ተጠቃሚ አንዲሆኑ በትኩረት እንደሚሰራ ገልፀዋል።

የእዣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘውዱ ዱላ በበኩላቸው፤ አካል ጉዳተኝነት በየትኛውም ቦታና ሁኔታ በሰው ልጆች ላይ ሊከሰት የሚችል ክሰተት እንደሆነ ገልጸው፤ ሰለሆነም አካል ጉዳኞችን መደገፍ አስፈላጊ መሆኑን አመላክተዋል።

በወረዳው ለአካል ጉዳተኞች በማህበር ከማደራጀት ጀምሮ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ በማንሳት በቀጣይም በዘርፉ አየተከናወነ የሚገኘው ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የጉራጌ ዞን አካል ጉዳተኞች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ አብይ ጀማል፤ በዞኑ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አካላት ጉዳተኞች እንዳሉ ገልፀዋል።

የበዓሉ መከበር ዋነኛ አላማ ለእነዚህ አካላት ክብር ለመስጠትና በሁሉም መስክ ላይ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እንደሆነ ጠቁመው፤ ለዚህ ውጤታማነት ደግሞ የአመራሩ ሚና ወሳኝ መሆኑን አመላክተዋል።

በመድረኩ የተነሱ ችግሮችን ለማረም ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት።

የበዓሉ ተሳታፊዎቸ በሰጡት አስተያየትም ከመድረኩ በቀጣይ ለስራቸው ስንቅ የሚሆን በርካታ ግብአቶችን ማግኘታቸውን ገልጸው፤ አካል ጉዳተኞች የትኛውንም ስራ በየትኛውም ቦታ መስራት እንደሚችሉ አሰረድተዋል።

በተለይም በቀጣይ ሁሉን አቀፉ ስራዎችን ለማከናወን መንግስት በየአካባቢው የሚገነቡ ህንጻዎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ ደጋጋ ሂሳቦ – ከወልቂጤ ጣቢያችን