“ዘ ስፔሻል ዋን” አስቀድመው ያዩት እውነት

“ዘ ስፔሻል ዋን” አስቀድመው ያዩት እውነት

በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ታሪክ ውስጥ እንደ ሆዜ ሞሪንሆ የእግር ኳስን ሂደት አስቀድሞ በማንበብና በጥቃቅን ታክቲካዊ ዝርዝሮች ላይ ትክክለኛ ግምገማ በመስጠት የሚታወቅ አሰልጣኝ ማግኘት ከባድ ነው።

እ.ኤ.አ. በ2020 ቶተንሃም በሰሜን ለንደን ደርቢ በአርሰናል ከተረታ በኋላ፣ “ዘ ስፔሻል ዋን“ የተናገሩት ንግግር ዛሬ ላይ ሆኖ ሲታይ ተራ የአሰልጣኝነት አስተያየት ሳይሆን አርሰናል ወደፊት የሚደርስበትን ደረጃ አስቀድሞ የተናገሩበት ትንቢታዊ እይታ ነበር።

በወቅቱ ሞሪንሆ ስለ ሚኬል አርቴታ እና አርሰናል ሲናገሩ “ለሚኬል እንኳን ደስ አለህ ለማለት እፈልጋለሁ። በታክቲክ በኩል በጣም፣ በጣም እያደጉና እየጠነከሩ መጥተዋል። እኔ በእግር ኳስ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ቆይቻለሁ፤ ሁኔታዎችን አስቀድሜ ማንበብ እችላለሁ። አርቴታ ድንቅ ሥራ እየሰራ ነው። ለወጣቶች ትልቅ እምነት ሰጥቷል፤ ተጫዋቾችን የሚመራበት ድንቅ ነው። ጊዜ እንዲሰጠው ተስፋ አደርጋለሁ፤ ለአርሰናል ደጋፊዎች የምናገረው፣ ከእሱ ጋር አርሰናል እንደገና ያ የቀደሞ አርሰናል ይሆናል!” ነበር ያሉት።

አርቴታ አርሰናልን በተረከበበት የመጀመሪያዎቹ ዓመታት የነበሩት ፈተናዎች ቀላል አልነበሩም።

ቡድኑ የነበረበት ዝቅተኛ ደረጃ፣ የውጤት መዋዠቅ እና የአመራር ክፍተቶች በደጋፊው ዘንድ ትልቅ ጥርጣሬን ፈጥረው ነበር።

ሆኖም ሞሪንሆ በወቅቱ የተመለከቱት ነገር ቢኖር የውጤቱን ማነስ ሳይሆን ቡድኑ በታክቲክ እና በባህሪ በኩል እያሳየ የመጣውን መሰረታዊ ለውጥ ነበር።

ዛሬ አርሰናል በሊጉ ብቻ ሳይሆን በኤውሮፓ መድረክ በጠንካራ የመከላከል እና የማጥቃት አወቃቀሩ የሚፈራ ቡድን ሆኗል።

ሞሪንሆ እንዳሉት አርቴታ እንደ ቡካዮ ሳካ፣ ገብርኤል ማርቲኔሊ፣ እና ማርቲን ኦዴጋርድ ያሉ ወጣቶችን የቡድኑ ዋና አከርካሪ በማድረግ ትልቅ ስኬት አስመዝግቧል።

አርሰናል አሁን ላይ ለፕሪሚየር ሊጉ ዋንጫ በየዓመቱ በዋናነት የሚፎካከር እና የሰሜን ለንደን የበላይነቱን ሙሉ በሙሉ ያስመለሰ ሀያል ቡድን መሆን ችሏል።

የሆዜ ሞሪንሆ ንግግር አርሰናል ለአርቴታ የሰጠው ጊዜ እና ትዕግስት ምን ያህል ትክክለኛ ውሳኔ እንደነበር የሚያስረግጥ ከመሆኑም በላይ፣ “ዘ ስፔሻል ዋን” አሁንም የእግር ኳስን የወደፊት ጉዞ አስቀድመው በማንበብ ረገድ ወደር የሌላቸው መሆናቸውን ሌላ ማረጋገጫ ሆኗል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ