‎በክረምት ወራት የሚካሄዱ ስፖርታዊ ውድድሮች ወጣቶች አልባሌ ስፍራ እንዳይውሉ ከማድረግ በተጓዳኝ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ምቹ እድል እየፈጠረ መሆኑ ተገለጸ

‎በክረምት ወራት የሚካሄዱ ስፖርታዊ ውድድሮች ወጣቶች አልባሌ ስፍራ እንዳይውሉ ከማድረግ በተጓዳኝ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ምቹ እድል እየፈጠረ መሆኑ ተገለጸ
‎
‎በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር ሲካሄድ የቆየው የክረምት ወራት የእግር ኳስ ሻምፒዮና ተጠናቋል።
‎
‎በከተማው በክረምት ወራት የሚከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት መካከል አንዱ የሆነው የእግር ኳስ ሻምፒዮና በስምንት ቀበሌያት መካከል ሲደረግ ቆይቶ ፍፃሜውን አግኝቷል።
‎
‎በማጠቃለያው መርሃግብር ላይ የተገኙት የከተማው ከንቲባ አቶ ብዙአየሁ ታደሰ በንግግራቸው፤ በከተማው በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚከናወኑ ተግባራት ሁለንተናዊ ልማት ለማምጣት እየተደረገ ያለውን ጥረት በእጅጉ እየደገፉ እንደሆነ ተናግረዋል።
‎
‎በዘርፉ የተሳተፉትን አካላት ያመሰገኑት ከንቲባው፤ ስፖርቱ ህዝባዊ መሠረት ይዞ ውጤታማ እንዲሆን የከተማው አስተዳደር ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
‎
‎የከተማው ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ዩኒት አስተባባሪ አቶ በረከት ፉላሳ ሻምፒዮናው ወጣቶች በክረምት ወራት ከአልባሌ ስፍራ አንዲታቀቡ ከማድረግ በተጓዳኝ ተተኪ ስፖርተኞችን ከማፍራት ረገድ ውጤታማ እንደነበረ ገልጸዋል።
‎
‎የፍፃሜ ጨዋታ በክቢቻ እና በቡሼ ቀበሌ መካከል የተደረገ ሲሆን ቡሼ አሸናፊ በመሆን ዋንጫ አንስቷል።
‎
‎ዘጋቢ: አማኑኤል ትዕግሥቱ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን